አካል ጉዳተኞችን ያካተተ የጤና ፖሊሲ ተግባራዊ እየተደረገ ነው - ጤና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
አካል ጉዳተኞችን ያካተተ የጤና ፖሊሲ ተግባራዊ እየተደረገ ነው - ጤና ሚኒስቴር
አሶሳ፤ ግንቦት 22/2017(ኢዜአ):- አካል ጉዳተኞችን ያካተተ የጤና ፖሊሲ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ "በአጋዥ ቴክኖሎጂ አለመቻልን እንግታ" በሚል መሪ ሃሳብ ዓመታዊ ሀገር አቀፍ የአጋዥ ቴክኖሎጂ ኮንፍረንስ በአሶሳ ከተማ እያካሄደ ነው።
መድረኩ የአካል ጉዳተኞች የአጋዥ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እና አጋዥ ቴክኖሎጂን ተደራሽ ለማድረግ ያለመ ነው።
በጤና ሚኒስቴር የሜዲካል አገልግሎት መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ኢሊባቡር ቡኖ በወቅቱ እንደተናገሩት፥ በሀገር አቀፍ ደረጃ አካል ጉዳተኞችን ያካተተ የጤና ፖሊሲ ተግባራዊ እየተደረገ ነው።
በመላ ሀገሪቱ ከ22 በላይ የአካል ጉዳተኞች የተሃድሶ ማዕከላት መኖራቸውን ገልፀው፤ በእነዚህ ማዕከላት ጭምር የአካል ጉዳተኞችን አጋዥ ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች የአቅርቦት እጥረት ለመቅረፍ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ይህም አካል ጉዳተኞች አጋዥ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመው በሁሉም መስክ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል ነው ያሉት።
አካል ጉዳተኞች ሁሉንም የህክምና አገልግሎት በአንድ ቦታ እንዲያገኙ ከማድረግ በተጨማሪ ሰው ሰራሽ የአካል ድጋፍ በሀገር ውስጥ ማምረት ተችሏል ነው ያሉት።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ወልተጂ በጋሎ በበኩላቸው በክልሉ የጤና አገልግሎትን ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው።
በጤናው ዘርፍ የአካል ጉዳተኞች ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት ለማረጋገጥ የአሶሳ አካል ጉዳተኛ ተሃድሶ ማዕከልም አገልግሎት እየሰጠ ነው ብለዋል።
በቀጣይም አካል ጉዳተኞች የሚፈልጉትን አጋዥ ተክኖሎጂ እንዲያገኙ የባለድርሻ አካላት ዕገዛ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው መድረክ የጤና ሚኒስቴር አመራሮች፣ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን አመራሮች እንዲሁም ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ የጤና ቢሮ እና የአካል ጉዳተኞች ተሃድሶ ማዕከላት አመራሮች ተገኝተዋል።