ቀጥታ፡

ሁለተኛው ዙር የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) ክትባት በአዳማና ድሬዳዋ ከተሞች መሰጠት ተጀመረ

አዳማ/ድሬዳዋ፤ ግንቦት 22/2017(ኢዜአ)፦ ሁለተኛው ዙር የልጅነት ልምሻ(ፖሊዮ) መከላከያ ክትባት ዘመቻ በኦሮሚያ ክልል በአዳማ ከተማ እና በድሬዳዋ አስተዳደር መሰጠት ተጀምሯል።

በኦሮሚያ ክልል በሁለተኛው ዙር የተቀናጀ የልጅነት ልምሻ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ 8 ነጥብ 6 ሚሊዮን ህፃናትን ተደራሽ ለማድረግ ታቅዷል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሃይሉ በአዳማ በተካሄደው የክትባት ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ላይ እንዳሉት ኢንስቲትዩቱ የወረርሽኝና ተላላፊ በሽታዎችን ጨምሮ የተቀናጀ የበሽታ ቅኝትና ምላሽ ላይ እየሰራ ይገኛል።

የልጅነት ልምሻ መከላከያ ክትባትን ከመስጠት ጎን ለጎን የወባ፣ የኮሌራና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን ምልክት የመለየት ስራ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ተስፋዬ ክበበው በበኩላቸው በክልሉ የልጅነት ልምሻን ጨምሮ ሌሎች በሽታዎችን መከላከል የሚያስችል ክትባት በዘመቻና በመደበኛ ሁኔታ እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

በመጀመሪያው ዙር የተቀናጀ የልጅነት ልምሻ ክትባት ዘመቻ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ 8 ነጥብ 4 ሚሊዮን ህፃናትን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ገልፀው በሁለተኛው ዙር የክትባት ዘመቻ በአንደኛው ዙር የተከተቡትን ጨምሮ 8 ነጥብ 6 ሚሊዮን ህፃናትን ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱንም አስረድተዋል።

በሁለተኛው ዙር የልጅነት ልምሻ መከላከያ ክትባት ዘመቻ በክልሉ ከ20ሺህ በላይ የጤና ባለሙያዎች እንደሚሳተፉም ታውቋል።

በተመሳሳይ በድሬዳዋ አስተዳደር ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ከ83ሺህ በላይ ህፃናትን ተደራሽ የሚያደርገው ሁለተኛው ዙር የተቀናጀ የልጅነት ልምሻ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ዛሬ ተጀምሯል።

በከተማ አስተዳደሩ ለአራት ተከታታይ ቀናት ከሚካሄደው የክትባት ዘመቻ ጎን ለጎን የእናቶችና ህፃናት ጤናን የመጠበቅና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን የመከላከል ስራዎች እንደሚሰሩ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም