ቀጥታ፡

በጅማ የኮሪደር ልማት የትራፊክ እንቅስቃሴን ከማሳለጥ በላይ ለስራ እድል ፈጠራ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል

ጅማ፣ግንቦት 22/2017 (ኢዜአ) ፡-በጅማ ከተማ የኮሪደር ልማት የትራፊክ እንቅስቃሴን  ከማሳለጥ በላይ ለስራ እድል ፈጠራ ምቹ  ሁኔታ የፈጠረ  መሆኑን የከተማው ነዋሪዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት  ያነጋገራቸው  የከተማው ነዋሪዎች እንዳሉት የጅማ ከተማ የኮሪደር ልማት ከተማዋን ጽዱ፣ ውብ እና ምቹ በማድረግ አዲስ ገጽታ አላብሷታል።


 

የኮሪደር ልማቱን ተከትሎ የተሰሩ ካፍቴሪያዎችና ሱቆች ጭምር ለዜጎች ተጨማሪ የስራ እድል የፈጠሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በከተማው በተገነባው የኮሪደር ልማት ምክንያት በዘመናዊ ቡና መሸጫ ካፌ ስራ የተሰማሩት አቶ መከረም አባዲጋ፤ ''በከተማዋ በርካታ እንግዶች ስለሚመጡ የጅማን ቡና የሚያጣጥሙበት ስራ ፈጥረናል'' ብለዋል።


 

ይህም ከኮሪደር ልማቱ ጋር ተያይዞ የመጣ ንግድ መሆኑን በመግለጽ በርካታ የስራ እድሎችን ይዞ የመጣ መሆኑን ተናግረዋል።

በኮሪደር ልማቱ የከተማዋ መንገዶች በመስፋታቸውና ለትራፊክ እንቅስቃሴ ምቹ መሆናቸውን ጠቁመው በተለይም የእግር ጉዞ ለማድረግ የተመቸ እና የትራፊክ ሂደቱን የሚያሳልጥ በመሆኑ የአደጋ ስጋትንም የቀነሰ መሆኑን ተናግረዋል።

ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ አብዱረዛቅ ናስር፤ በኮሪደር ልማቱ መንገዶቹ መስፋታቸውና የእግረኛና የተሽከርካሪ እንዲሁም የሳይክል መንገድ መለየቱ የአደጋ ስጋትን በእጅጉ የቀነሰ መሆኑን ገልጸዋል።

ጅማ በእንጨት ውጤቶች፣ በቡና ምርት እንዲሁም በማርና በቅቤ የምትታወቅ በመሆኗ ይህንኑ የሚያቀርቡ በዚህ ንግድ የተሰማሩ ነዋሪዎችም በርካታ መሆናቸውን ጠቁመዋል።


 

የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ ጣሃ ቀመር፤ ከተማዋን ለማስዋብና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ የኮሪደር ልማቱ እየተተገበረ መሆኑን ተናግረዋል።

የኮሪደር ልማት ስራው በፍጥነት እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት ከንቲባው ለዚህም የከተማው ህብረተሰብ ለልማቱ ተባባሪና አጋዥ ሆኗል ብለዋል።

በኮሪደር ልማት ስራው በርካታ የስራ እድል መፈጠሩን ያነሱት  ከንቲባው ጅማ ለኢንቨስትመንት እና ለጎብኝዎች ማራኪ ትሆን ዘንድ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኮሪደር ልማቱ የመጀመሪያው ምእራፍ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም