ቀጥታ፡

አሰባሳቢ ትርክትን ለማስረጽ በተሰራው ስራ ውጤት ተመዝግቧል

ወላይታ ሶዶ፤ ግንቦት 22/2017(ኢዜአ)፦ በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ አሰባሳቢ ትርክትን ለማስረጽ በተሰራ ስራ ውጤት መመዝገቡን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ ተናገሩ።

ሚኒስትር ዴኤታው ''የድህረ እውነት ዘመንን በእውነት እና በእውቀት'' በሚል መሪ ሃሳብ ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚዲያ አመራሮችና ባለሙያዎች ስልጠና በሰጡበት ወቅት መገናኛ ብዙሃን እውነትን ይዘው ተጽዕኖ ፈጣሪነታቸውን ለማረጋገጥ መስራት አለባቸው ብለዋል።


 

ዘመኑ እውነት የተፈተነችበትና ስሜት ቀስቃሽ አጀንዳዎች ገነው የሚታዩበት በመሆኑ የሀሰት መረጃዎችን ለመከላከል ተጨማሪ አቅም ማጎልበት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጠንካራ ኢኮኖሚ የገነባችና ህብረ ብሔራዊነቷ የተጠበቀ ሀገር ለመገንባት ገዢ ትርክትን ማስረጽ የሚያስችል የሚዲያ ስራ መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል።

በዚህም የሚዲያ ዘርፉ ባለፉት ሁለት ዓመታት ብሔራዊ ትርክትን በማስረጽ በኩል አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

የሚዲያ ባለሙያዎችና አመራሮች የኢትዮጵያን እውነታና በብዝሃነት ውስጥ ያለውን ህብር እና ውበት አጉልተው እንዲያወጡ አቅም የማጎልበቱ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ሁሉም የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች ማህበራዊ ሚዲያዎችን ብሔራዊ ገዢ ትርክትን ለማስረጽ መጠቀም እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የዲላ ዙሪያ ወረዳ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሪፖርተር አትክልት ሲሳይ በየጊዜው የሚፈበረኩ ሀሰተኛ መረጃዎች የሚዲያን ተዓማኒነት ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ይህን ለመቀልበስም ሙያዊ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በወላይታ ዞን የዳሞት ወይዴ ወረዳ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዳንኤል ፋልታሞ በበኩላቸው ሀቅ ላይ ተመስርተን ዘመኑን የዋጀ የኮሙኒኬሽን ስራ እንድንሰራ የሚያግዝ አቅም በስልጠናው አግኝተናል ብለዋል።

በመሆኑም ለብሔራዊ ትርክት ግንባታ የበኩላቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም