ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከደለል መጠበቅ የሁሉም ዜጋ ሃላፊነት ነው - ጽህፈት ቤቱ - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከደለል መጠበቅ የሁሉም ዜጋ ሃላፊነት ነው - ጽህፈት ቤቱ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 22/2017(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ከደለል ለመጠበቅ በሚከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የሲቪክ ማህበራት እገዛቸውን ማጠናከር እንደሚገባቸው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስገነዘበ፡፡
ጽህፈት ቤቱ "አንድ እቅድ አንድ ሪፖርት ለተቀናጀ የአባይ ተፋሰስ ልማት የሲቪክ ማህበራት ሚና" በሚል መሪ ሃሳብ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምክክር እያካሄደ ነው።
በዚሁ ወቅት የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሄ(ዶ/ር) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን ከድህነት ለመላቀቅ ያላቸውን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳዩበት ትልቅ ሀገራዊ ሀብት መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ማህበረሰቡ፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ዘርፈ ብዙ ድጋፍ በማድረግ ግድቡን ወደ ማጠናቀቂያ ምዕራፍ ማሸጋገር መቻላቸውን አስረድተዋል።
የህዳሴ ግድቡ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የልማት ዕድገት የሚኖረውን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ከወዲሁ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ነው ያስታወቁት።
ለዚህ ደግሞ የታላቁ የህዳሴ ግድብ በደለል እንዳይሞላ እንደሀገር በሚሰሩ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራዎች ላይ መሳተፍ የሁሉም ዜጋ ሃላፊነት መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው ውጤታማ እንዲሆን የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች በዘርፉ ያላቸውን አበርክቶ በተደራጀ እና በተቀናጀ መልኩ እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።