በባህል፣ ቋንቋና ቴክኖሎጂ መካከል ያለውን ትስስር በማጎልበት ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በባህል፣ ቋንቋና ቴክኖሎጂ መካከል ያለውን ትስስር በማጎልበት ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ ይገባል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 22/2017(ኢዜአ)፦ በባህል፣ ቋንቋና ቴክኖሎጂ መካከል ያለውን ትስስር በማጎልበት ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ።
ቢሮው፣ ከኢንፎርሜሽንና መረብ ደህንነት አስተዳደር እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጋራ በመተባበር ሁለተኛውን ከተማ አቀፍ የቋንቋና የባህል ጉባኤ እያካሄደ ይገኛል።
ጉባዔው “ባህል፣ ቋንቋ እና ቴክኖሎጂ ለዕድገት” በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው።
በዚሁ ወቅት የቢሮው ኃላፊ ሂሩት ካሳው(ዶ/ር)፤ ባህልና ቋንቋ የአንድ ማህበረሰብ የማንነት መገለጫ ከመሆናቸው ባለፈ ማህበራዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ እሴቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ባህላዊ እሴቶች ለቴክኖሎጂ ፈጠራና በዓለም ዙሪያ ለተገኙ ለውጦች መሰረት መሆናቸውን ጠቅሰው ቴክኖሎጂ ዓለምን አንድ ያደረገ አገናኝ ድልድይ ነው ብለዋል።
ሀገራችን የብዝሃ ባህልና ቋንቋ ባለቤት በመሆኗ ቋንቋንና ባህልን ከቴክኖሎጂ ጋር በማስተሳሰር ለዘላቂ ልማት ማዋል እንደሚገባ ነው የተናገሩት።
በባህላዊ እሴቶችና ዕውቀቶች እንዲሁም በባህል፣ ቋንቋና ቴክኖሎጂ መካከል ያለውን ትስስር በማጎልበት ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአለም አቀፍ ግንኙነትና ትብብር ዳይሬክተርና የፕሬዝዳንቱ ተወካይ ራሄል አርጋው(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ ከተለያዩ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የባህልና ቋንቋዎች ጥናት ማዕከል በቋንቋና ባህል ዘርፍ ውጤታማ ስራ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው ማዕከሉ ቋንቋና ባህል ከቴክኖሎጂ ጋር ማዘመን የሚያስችሉ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
የባህልና ቋንቋ እሴቶችን ጨምሮ የተለያዩ የምርምር ውጤቶችን በቴክኖሎጂ መሰነድ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለውም ጠቁመዋል።
በመርኃ ግብሩ ቋንቋና ባህልን ዘመኑ በደረሰበት ቴክኖሎጂ ለማስደገፍ የሚረዱ የጥናት ውጤቶች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ተገልጿል።