ሀገራዊ ምክክሩ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠርና የተሻለች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስተላለፍ የላቀ ድርሻ አለው - ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ(ፕ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠርና የተሻለች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስተላለፍ የላቀ ድርሻ አለው - ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ(ፕ/ር)
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 22/2017(ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ምክክሩ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠርና የተሻለች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስተላለፍ የላቀ ድርሻ እንዳለው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ(ፕ/ር) ገለጹ።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የፌዴራል ተቋማትና የማህበራት የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው።
በምክክር ሂደቱ ከ38 ተቋማትና ማህበራት ተወካዮች በመሣተፍ ላይ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ኢትዮጵያ የነጻነት ተምሣሌት ፋና ወጊ የበርካታ ቋንቋ፣ ባህል እና እሴት ሀገር ናት ብለዋል።
ሀገራዊ ምክክር የሃሳብ ልዩነቶችን ተቀራርቦ በውይይት መፍታት የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ ዛሬ በፌደራል ተቋማትና ማህበራት ደረጃ እያካሄደ የሚገኘው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ 14ኛ መድረክ መሆኑንም ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል የምክክር ሂደትን ማካሄድ እንዲሁም በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ እንደሚቀሩትም ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ ወደ ዋናው የምክክር ሂደት ለመግባት የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ በጉዞው አካታችነትና አሳታፊነትን ተግባራዊ እያደረገ መምጣቱን ተናግረዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠርና የተሻለች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስተላለፍ የላቀ ድርሻ እንዳለውም ነው ዋና ኮሚሽነሩ የተናገሩት።
ሀገራዊ ምክክሩ በኢትዮጵያ ስር የሰደዱ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ጉልህ ሚና ያለው መሆኑንም ጠቁመዋል።
ዛሬ የተጀመረው የምክክር ምዕራፍ እስከ ግንቦት 24 ቀን 2017 ድረስ የሚቆይ ይሆናል።