ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክሩ ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ ነው - ዋና ኮሚሽነር መሥፍን አርአያ(ፕ/ር)

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 22/2017(ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ምክክሩ ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መሥፍን አርአያ(ፕ/ር) ገለጹ።

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የፌዴራል ተቋማትና ማህበራት የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ በአዲስ አበባ ማካሄድ ጀምሯል።

በመድረኩ የፌዴራል መንግስት ተወካዮች፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከተለያዩ ማህበራት እና ፌዴሬሽኖች፣ የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች፣ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ የመከላከያ ሰራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የፌዴራል ፍርድ ቤት፣ የፌዴራል ንግድ ምክር ቤትን ጨምሮ ሌሎች ተወካዮች በመሣተፍ ላይ ይገኛሉ።


 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መሥፍን አርአያ(ፕ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት ሀገራዊ ምክክሩ ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ በመሆኑ በንቃት መሳተፍ ይገባል ብለዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠርና የተሻለች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስተላለፍ የላቀ ድርሻ እንዳለውም ተገልጿል።

በሀገሪቱ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ጉልህ ሚና ያለው መሆኑም እንዲሁ።

ዛሬ የተጀመረው የምክክር ምዕራፍ እስከ ግንቦት 24 ቀን 2017 ዓም የሚካሄድ ሲሆን፤ በምክክር ሂደቱ 38 ተቋማትና ማህበራትን የሚወክሉ ተወካዮች ይሳተፋሉ።

ኮሚሽኑ በእስካሁን ሂደቱ በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍን የተገበረ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 በተሰጠው ስልጣንና ሀላፊነት መሰረት የምክክር አጀንዳዎችን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት በህዝባዊ ውይይቶችና ሌሎች አግባብነት ባላቸው መንገዶች እየሰበሰበ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም