የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 22/2017 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 32ኛ ሳምንት ዛሬም ቀጥሎ ሲውል ሁለት ጨዋታዎች በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይካሄዳሉ።
ስሑል ሽሬ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።
ባለፉት 12 የሊግ ጨዋታዎች ከድል የራቀው ስሑል ሽሬ በ22 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
በሊጉ ባለፉት ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት ያስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ40 ነጥብ 8ኛ ደረጃን ይዟል።
የስሑል ሽሬ ማሸነፍ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት በሚያደርገው ፉክክር ስንቅ የሚሆን ሶስት ነጥብ ያስገኝለታል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ የዛሬው ጨዋታ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርገው ነው።
በሌላኛው የ32ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከድሬዳዋ ከተማ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የአምናው የሊጉ አሸናፊ ንግድ ባንክ በ39 ነጥብ 9ኛ ደረጃን ይዟል። ድሬዳዋ ከተማ በ36 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ባለፉት ስድስት የሊግ ጨዋታዎች ድል ያልቀናው ንግድ ባንክ ማሸነፍ ወደ ድል መንገድ ይመልሰዋል።
ድሬዳዋ ከተማ ካሸነፈ ከመውረድ ስጋት የመላቀቅ እድሉን ይበልጥ ያሰፋል።