ቀጥታ፡

ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስከብሩና ቀጣናዊ ትብብርን የሚያጠናክሩ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - አምባሳደር ሽብሩ ማሞ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 21/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብሩና ቀጣናዊ ትብብርን የሚያጠናክሩ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ሽብሩ ማሞ ገለጹ።

ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ዜጎች የምትሰጠው የትምህርት ዕድልና የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ጠንካራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መፍጠራቸውን አንስተዋል።

አምባሳደር ሽብሩ ማሞ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ የሀገራትን የህዝብ ለህዝብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር በማስተሳሰር የመንግስታትን ትብብር የሚያሳልጥ የዲፕሎማሲ ስልት ነው ብለዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿና ሌሎች ሀገራት ህዝቦች ጋር ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎትን የሚያስገነዝቡ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና ገጽታ ግንባታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሚፈጠር የትብብር ግንኙነትም የህዝብ ለህዝብ የልምድና ተሞክሮ ልውውጥ እየተፈጠረ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እየተመዘገቡ የሚገኙ ፈጣን የኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ ለውጦች ለሀገር ገጽታ ግንባታ የማይተካ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ አብራርተዋል።

በአዲስ አበባ የተሰሩ የኮሪደር ልማት ስራዎች መዲናዋን ለቱሪዝም ኮንፍረንስ ምቹ በማድረግ ኢትዮጵያና አፍሪካን በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ከቀሪው ዓለም ጋር እያስተሳሰሩ እንደሚኙም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ቅድሚያ ለጎረቤት ይሰጣል ያሉት አምባሳደሩ በዚህም በፓርላማ፣ በምሁራንና በተማሪዎች፣ በማህበራትና በኪነ-ጥበብ ሙያተኞች ከጎረቤት ሀገራት ጋር በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ስኬታማ ስራ መስራቱን ገልጸዋል።

በፐብሊክ ዲፕሎማሲ የተሰራው ስኬታማ ስራ ለሀገር ብሔራዊ ጥቅም መከበርና ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ መሳካት ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከቱን አስረድተዋል።

ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን ሁለተኛ የዓድዋ ድል ነው ያሉት አምባሳድር ሽብሩ በግድቡ ግንባታ ሂደትም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ያላሳለሰ ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

በዓለም አቀፍ መድረኮች በግድቡ ግንባታ ላይ የሚደረጉ ጫናዎችን ለመቀልበስ በተከናወነ የዲፕሎማሲ ስራ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የሀገራቸውን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቃቸውን ነው ያብራሩት።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ዜጎች የምትሰጠው የትምህርት ዕድልና የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትንና ቀጣናዊ ትብብርን እያጠናከረ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿና ሌሎች ሀገራት ጋር ያላትን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ በማጠናከር በመሰረተ ልማት፣ በስፖርትና በሌሎች ዘርፎች የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ለማጠናከር በትኩረት እንደምትሰራ አረጋግጠዋል።

በውጭ የሚኖሩ ዜጎች የኢትዮጵያን ባህልና እሴት በዓለም አደባባይ በማስተዋወቅ ለሀገር ብሔራዊ ጥቅም መከበር ጉልህ ሚና እየተወጡ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም