በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚከናወኑ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን ወደ ተግባር ለመቀየር የተጀመረው ስራ ይጠናከራል - ሚኒስቴሩ - ኢዜአ አማርኛ
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚከናወኑ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን ወደ ተግባር ለመቀየር የተጀመረው ስራ ይጠናከራል - ሚኒስቴሩ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 21/2017(ኢዜአ)፦ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚከናወኑ ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን ወደ ተግባር ለመቀየር የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጡሹኔ ገለጹ።
በቅድስተ ማርያም ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት የሚካሄደው 23ኛው የአፍሪካ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዓለም አቀፍ ጉባኤ " የምርምር ስራዎች ለለውጥና ለልማት" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በጉባኤው የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጡሹኔን ጨምሮ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን፣ ከአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ህብረት እና ከአፍሪካ የከፍተኛ ትምህርት ዓለም አቀፍ ኔትወርክ የተጋበዙ አመራሮችና ተወካዮች ተገኝተዋል።
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጡሽኔ በዚህ ወቅት እንዳሉት በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በርካታ የሪፎርም ስራዎች ተሰርተዋል።
በመንግስት እና በግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚከናወኑ የጥናትና የምርምር ስራዎችን ጥራት ሊያሻሽሉ የሚችሉ የድጋፍና ክትትል ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የጥናትና ምርምር ስራዎቹን ወደ ተግባር መለወጥ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሃላፊነት በመሆኑ የተጀመረው የቅንጅት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚሰሩ ምርምሮች በኢትዮጵያ በመከናወን ላይ ለሚገኙ የልማት ስራዎች በግብዓትነት ሊያገለግሉ እንደሚገባም አንስተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚደረጉ የጥናትና ምርምር ስራዎች ምን ያህል ችግር ፈቺ ናቸው የሚለው እየተለካ መሆኑን አንስተዋል።
በዚህ ሂደት በተለይም የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ወደ ተግባር መግባታቸውን ጠቅሰው የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በጥናትና ምርምር ላይ በትኩረት እንዲሰሩ የአቅም ግንባታ ስራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
የቅድስተ ማርያም ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ተባባሪ ፕሮፌሰር ወንድወሰን ታምራት ባለፉት 23 አመታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልፀዋል።
በዚህም መንግስት ለሚያዘጋጃቸው ፖሊሲና ስትራቴጂዎች በግብዓትነት የሚውሉ የምርምር ስራዎች ተሰርተዋል ነው ያሉት።
ኮንፍረንሱ በኢትዮጵያ የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከአለም አቀፍ የትምህርት ተቋማት ልምድ እንዲቀስሙ ያስችላል ብለዋል።
በኦርጋናይዜሽን ኦፍ ሳውዝ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ የሪሰርችና የፖሊሲ ባለሙያው አንድሪው ደመስ በበኩላቸው አፍሪካውያን መሰረታዊ ችግሮቻችንን ለመፍታት የሚረዱ የጥናትና ምርምር ስራዎቻችን በጋራ ልንሰራ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።
ኮንፍረንሱ የጋራ የሆኑ ችግሮችን በጥናትና ምርምር በማስደገፍ መፍታት እንደሚያስችልም ተናግረዋል።
በጉባኤው ከአፍሪካ፣ ከእስያ፣ ከአውሮፓ እና ከላቲን አሜሪካ የተጋበዙ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።