ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ለመስጠት በአረንጓዴና ዘላቂ ልማት ላይ በቁርጠኝነት እየሰራች ነው - የፕላንና ልማት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ለመስጠት በአረንጓዴና ዘላቂ ልማት ላይ በቁርጠኝነት እየሰራች ነው - የፕላንና ልማት ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 21/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ለመስጠት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ሀገሪቱ ለአረንጓዴና ዘላቂ ልማት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳዩ መሆናቸውን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ገለፀ።
በፕላንና ልማት ሚኒስቴር አዘጋጅነትና በአዲስ አበባ የኖርዌይ እና እንግሊዝ ኤምባሲዎች ትብብር የተዘጋጀ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ፎረም ቴክኒካል ቡድን ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ የመንግስት አካላት፣ የልማት አጋሮች እና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡
በመድረኩ ጳጉሜ 2017 ዓም በአዲስ አበባ በሚካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባዔ ዙሪያ ውይይት ተደርጓል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የአየር ንብረት ለውጥ የወደፊት ስጋት ብቻ ሳይሆን አሁን ላይ ችግሮችን እያስከተለ ያለ አለም አቀፍ ክስተት ነው።
ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ፣ የታዳሽ ኃይል፣ የአረንጓዴ ትራንስፖርት እና ሌሎች የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነች መሆኗን ተናግረዋል።
በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባዔ እንድታዘጋጅ መመረጧንና ጉባዔው የአየር ንብረት ለውጥ ፈተናን ለመቋቋም የሚመክር እንደሚሆንም ተናግረዋል።
አፍሪካ የአለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄዎችን በማቅረብ የመሪነት ሚናዋን ልትወጣ ይገባልም ነው ያሉት።
ጉባዔው በኢትዮጵያ እና በመላው አፍሪካ እየተከናወኑ ያሉ በርካታ የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም የሚያስችሉ ስራዎችን ለማሳየት ያስችላል ብለዋል።
በሚኒስቴሩ የአየር ንብረት ተቋማዊ ልማት አማካሪ መንሱር ደሴ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ መስጠት የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች።
ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ፎረም ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ እየሰራች ላለው ተግባር ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን አንስተው ፎረሙ በየሩብ አመቱ ተገናኝቶ እንደሚመክር ተናግረዋል።
መድረኩ ጳጉሜ 2017 የሚካሄደውን ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባዔ በተመለከተ ለመምከር የተዘጋጀ መሆኑንም ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ የኖርዌይ ኤምባሲ የአየር ንብረት አማካሪ ሊቭ ሳይደንስ በበኩላቸው፤ ኖርዌይ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር በቅንጅት እየሰራች ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በካርበን ሽያጭ ላይ እያከናወነች ላለው ተግባር ድጋፍ እያደረግን ነው ያሉት ደግሞ የእንግሊዝ ኤምባሲ የውጭና የጋራ ልማት ፅህፈት ቤት የአየር ንብረትና ተፈጥሮ ሀብት ኃላፊ ኒና ሂሰን(ዶ/ር ) ናቸው።
አንደኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባዔ ከሁለት አመት በፊት በኬንያ መካሄዱ ይታወሳል።