በኮሪደር ልማት የተገነቡ የመንገድ መሠረተ ልማቶቹ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው

አዲስ አበባ፤ግንቦት 21/2017 (ኢዜአ)፦በኮሪደር ልማት የተገነቡ የመንገድ መሠረተ ልማቶቹ የትራንስፖርት እንቅስቃሴን በማሳለጥ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ ገለጸ።

ቢሮው ”በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሪደር ልማት ያስገኛቸውን የትራንስፓርት መሰረተ ልማት መልካም አጋጣሚዎች በአግባቡ መጠቀምና ማስተዳደር” በሚል መሪ ሃሳብ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያካሄደ ነው።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ወርቁ ደስታ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ አስተዳደሩ መዲናዋን ስማርት ከተማ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ ይገኛል።

በዚህም በመዲናዋ ሰፊ የኮሪደር ልማት እና የመልሶ ግንባታ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፥ ግንባታዎቹ ውጤታማና ዘላቂ የትራንስፖርት ሥርዓት ለመዘርጋት ትልቅ ሚና እንዳላቸው አስረድተዋል።




የልማት ሥራዎቹ ዘመናዊ የትራንስፖርት መሰረተ ልማትን ያሟሉና ደረጃቸውን የጠበቁ የመኪና፣የእግረኛና የብስክሌት መንገድ ፣የመኪና ማቆሚያ ተርሚናሎች እና የትራፊክ ምልክቶችን ማካተታቸውን ጠቅሰዋል።

የመንገድ መሠረተ ልማቶቹ የትራንስፖርት እንቅስቃሴን በማሳለጥ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው ብለዋል።

የትራንስፖርት መሰረተ ልማቶቹ የተፈለገውን አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ በአግባቡ መጠቀም እና ማስተዳደር አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

ቢሮው ተገልጋዮች በተዘረጉት መሰረተ ልማቶች በአግባባቡ እንዲጠቀሙ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎች ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም