ደም ለሚሹ ወገኖች ለመድረስ ደም የመለገስ ባህላችንን ልናጎለብት ይገባል-የኢዜአ ሠራተኞች - ኢዜአ አማርኛ
ደም ለሚሹ ወገኖች ለመድረስ ደም የመለገስ ባህላችንን ልናጎለብት ይገባል-የኢዜአ ሠራተኞች
አዲስ አበባ፤ግንቦት 21/2017 (ኢዜአ)፦በተለያየ የጤና እክል ምክንያት ደም ለሚሹ ወገኖች ለመድረስ በመደበኛነት ደም የመለገስ ባህላችንን ልናጎለብት ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አመራርና ሰራተኞች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አመራርና ሠራተኞች ዛሬ ለ14ኛ ጊዜ የደም ልገሳ መርሀ ግብር አካሂደዋል።
በኢዜአ የሴቶች እና ባለብዙ ዘርፍ ዳይሬክተር ታደለች ቦጋለ በዚህ ወቅት፥ ኢዜአ ከመደበኛው ስራ ባለፈ ማህበራዊ ሃላፊነቱን መወጣት በሚያስችሉ ተግባራት ላይ በንቃት እየተሳተፈ መሆኑን ገልጸዋል።
የተቋሙ ሠራተኞችም በየሦስት ወሩ ደማቸውን በመደበኛነት በመለገስ ሰብዓዊ ተግባር እየፈጸሙ መሆናቸውንም አንስተዋል።
በኢዜአ የክልሎች ክላስተር ግንኙነት ቡድን መሪ ዮሃንስ ወንድይራድ ዛሬ ለ14ኛ ጊዜ ደም መለገሳቸውን ተናግረዋል።
በህክምና ወቅት ደም ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች መድረስ የሚያስችላቸውን ሰብአዊ ተግባር በማከናወናቸው የህሊና እርካታ እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል።
"ደም መለገስ ህይወትን ማዳን ነው" ያለችው ደግሞ በኢዜአ የነጋሪ መፅሔት ምክትል ዋና አዘጋጅ የሺመቤት ደመቀ ናት።
በተለያዩ አደጋዎች ደም ማግኘት ባለመቻላቸው ምክንያት ለከፋ አደጋ ሊጋለጡ የሚችሉ ዜጎቻችንን ህይወት ለመታደግ ደም የመለገስን ተግባር ማጠናከር እንደሚገባ አንስታለች።
በኢዜአ የዲጂታል ሚዲያ የሀገር ውስጥ ቋንቋ አዘጋጅ ሙሴ መለሰ በበኩሉ፥ ደም መለገስ ለህሙማን ጤና ከመድረስ ባለፈ ለደም ለጋሾች በብዙ መልኩ ጠቃሚ መሆኑን ተናግሯል።
ተቋማት የደም ልገሳ መርሀ ግብሮችን ከማጠናከር ባለፈ ደም ልገሳን በተመለከተ የግንዛቤ ስራዎችን ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁሟል።