በኦሮሚያ ክልል የተከናወነው የአፈርና የውሃ ጥበቃ ስራ የተጎዳ መሬትን ወደ ልማት እንዲገባ እያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል የተከናወነው የአፈርና የውሃ ጥበቃ ስራ የተጎዳ መሬትን ወደ ልማት እንዲገባ እያደረገ ነው

አዳማ ፤ግንቦት 21/2017 (ኢዜአ)፡-በኦሮሚያ ክልል የተከናወነው የአፈርና የውሃ ጥበቃ ስራ የተጎዳ መሬትን ወደ ልማት እንዲገባ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ሀላፊ ኤሊያስ ከድር፤ በዘንድሮ የበጋ ወቅት ህብረተሰቡን በማሳተፍ 3 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎቹ ከዚህ ቀደም ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው መሬቶችን ወደ ልማት ለማስገበት ትልቅ እገዛ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም በሀረርጌ አካባቢ የተሰራው የተፋሰስ ልማት ስራ ተራሮችን ከማስዋብ ባለፈ የአካባቢው አርሶ አደሮች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የጀመሩትን ስራ እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ የለሙ የአፈርና ውህ ጥበቃ ስራዎች የአካባቢን ስነ-ምህዳር ከመጠበቃቸው ባለፈ የከርሰ ምድርና ገጸ ምድር ውሀ ሀብቶች እንዲጨምሩ ማድረጉን አስታውሰዋል።
የተፋሰስ ልማት ስራ በክልሉ ከዚህ ቀደም በስፋት በማይተገበርባቸው አካባቢዎች ጭምር በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፥ ለአብነትም ጅማ ዞንን አንስተዋል።
በዚህም በጋ ወራት የተፋሰስ ልማት ስራው በተከናወነባቸው መሬቶች ላይ በክረምቱ ወቅት ደግሞ በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ችግኞችን መትከል የችግኝ መትከያ ጉድጓድ ዝግጅት እየተከናወነ ይገኛልም ብለዋል።
በጅማ ዞን በተፋሰስ ልማት ላይ ከተሳተፉ አርሶ አደሮች መካከል ረሻድ አባቡልጉ፤ላለፉት ሶስት ወራት ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በመተባበር በጎርፍ የተጎዱ አካባቢዎች ላይ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ ማከናወናቸውን ተናግረዋል።
ቀደም ባሉት አመታትም የተራቆቱ አካባቢዎች ላይ የእርከን ስራዎችን በመስራት በጎርፍ ሲሸርሸር የነበረ መሬትን ከአፈር መከላት መከላከል እንደተቻለ ገለጸዋል።
ቀደም ሲል ለአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራዎች ትኩረት ባለመሰጠቱ ተዳፋታማ መሬቶች ለአፈር መሸርሸር በመጋለጥ የምርት መቀነስ አጋጥሟቸው እንደነበረ የተናገሩት ደግሞ ሌላው የጅማ ዞን አርሶ አደር ሙላቱ ጋሻው ናቸው።
ችግሩን ለመከላከልም ባለፉት አመታት መንግስት የቀየሰውን የአፈርና የውሃ ጥበቃ ስራ በማከናወን ምርታማነታቸው እንዲጨምር ማድረጉን ተናግረዋል።