በከተማ አቀፉ ፈተና ጥሩ ውጤት በማስመዝገብ ወደ ቀጣይ ክፍል ለመሸጋገር በአግባቡ እየተዘጋጀን ነው-ተማሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በከተማ አቀፉ ፈተና ጥሩ ውጤት በማስመዝገብ ወደ ቀጣይ ክፍል ለመሸጋገር በአግባቡ እየተዘጋጀን ነው-ተማሪዎች

አዲስ አበባ፤ግንቦት 21/2017(ኢዜአ)፦በከተማ አቀፉ ፈተና ጥሩ ውጤት በማስመዝገብ ወደ ቀጣይ ክፍል ለመሸጋገር በአግባቡ እየተዘጋጁ መሆኑን የስድስተኛ እና የስምንተኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ የ2017 ዓ.ም የስምንተኛ እና የስድስተኛ ክፍል ተማሪዎች ከተማ አቀፍ ፈተና በሰኔ ወር እንደሚሰጥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ያወጣው ፕሮግራም ያሳያል።
በዚህም መሰረት ሰኔ 3 እና 4 የስምንተኛ ክፍል እንዲሁም ከሰኔ 10 እስከ ሰኔ 12 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ የስድስተኛ ክፍል ተማሪዎች ፈተናውን ይወስዳሉ።
ኢዜአ ተፈታኝ ተማሪዎች በምን መልኩ ዝግጅት እያደረጉ ነው ሲል በመዲናዋ በሚገኙ ሁለት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቅኝት አድርጓል።
ሜሮን ፍቅሬ በሰፈረ ሰላም ቅድመ አንደኛ ፣አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን ፈተናውን በጥሩ ውጤት በማለፍ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመሻገር ዝግጅት እያደረገች መሆኑን ተናግራለች።
በተለይም ፈተናው ከሚያካትታቸው የትምህርት አይነቶች አጫጭር ማስታወሻዎች በማውጣት በማጥናት ላይ እንደምትገኝም አክላለች።
በሰፈረ ሰላም ትምህርት ቤት የስድስተኛ ክፍል ተማሪው አቤል ገረመው በበኩሉ በቤቱ እና በትምህርት ቤት ለፈተናው የሚረዳውን አጋዥ መጽሃፍ በማንበብ ጥያቄዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኝ ተናግሯል።
በአሚጎንያን ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ወንጌላዊት ነቢያት ትምህርቴን፥ በአግባቡ በመከታተል ለከተማ አቀፍ ፈተናው እየተዘጋጀሁ ነው ብላለች።
ከዚህ ባለፈ የተለያዩ ጥያቄዎችን በመስራትና ያልገባትን ሃሳብ ከጓደኞቿ እና ከመምህራኖቿ በመጠየቅ ለፈተናው ዝግጀት በማድረግ ላይ መሆኗን ነው የተናገረችው።
በቀጣይ ዓመት ወደ ሰባተኛ ክፍል መሸጋገር የሚያስችላትን አመርቂ ውጤት ለማስመዝገብ በፕሮግራም እየተዘጋጀች መሆኗን የገለጸችው የዚሁ ትምህርት ቤት የስድስተኛ ክፍል ተማሪ እየሩሳሌም ግርማ ናት።
ተማሪ ሜሮን እና ተማሪ ወንጌላዊት የፈተናው እለት እስኪደርስ ድረስ የጀመሩትን ጥናት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸው፥ ሌሎች ተፈታኝ ተማሪዎችም ጊዜያቸውን በአግባቡ በመጠቀም እንዲያነቡ መክረዋል።
የሰፈረ ሰላም ቅድመ አንደኛ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህር እስጢፋኖስ ደሜ በበኩላቸው፥ ትምህርት ቤቱ በሁለቱም ደረጃዎች 494 ተማሪዎችን እንደሚያስፈትን ገልጸዋል።
ተማሪዎቹ በእውቀትና በስነልቦና ዝግጁ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የአሚጎንያን ትምህርት ቤቶች አካዳሚክ ዳይሬክተር ኤሳው አለማየሁ (ዶ/ር) የትምህርት ማህበረሰቡ አባላት ተማሪዎች በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ከወዲሁ አስፈላጊውን እገዛ ማድረግ አለብን ብለዋል።
በሰፈረ ሰላም ቅድመ አንደኛ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት የስምንተኛ ክፍል መምህርት ጠጅቱ ድሪባ፥ ትርፍ ጊዜአችንን በመጠቀም ተማሪዎቻችንን በሚገባው ልክ እያዘጋጀን ነው ብላለች፡፡
በአሚጎኒያን ትምህርት ቤት የሰባተኛ እና የስምንተኛ ክፍል መምህር ታደለ ዘሪሁን በበኩላቸው፥ ተማሪዎቻቸው ያልገባቸውን ጥያቄ በሚገባ እንዲረዱና ተገቢውን ዝግጅት እንዲያደርጉ በማገዝ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።