ቀጥታ፡

የፌዴራል ተቋማትና ማህበራት አጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረክ ስኬታማ እንዲሆን ሁሉም የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል-ኮሚሽኑ

አዲስ አበባ፤ግንቦት 21/2017(ኢዜአ)፦ነገ የሚጀመረው የፌዴራል ተቋማትና ማህበራት አጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረክ ስኬታማ እንዲሆን ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ።

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቃል አቀባይ ጥበቡ ታደሰ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ከነገ ግንቦት 22 እስከ 24 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ የፌዴራል ተቋማትና ማህበራት የአጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረክ ይካሄዳል።

በመድረኩ ከ38 የፌዴራል ተቋማትና ማህበራት የተወጣጡ 800 ተሳታፊዎች እንደሚገኙና ለጉባዔው ስኬታማነት የቅድመ ዝግጅት ስራ መሰራቱንም ተናግረዋል።

የምክክር ኮሚሽኑ እስካሁን 13 የአጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረኮች ማካሄዱን ጠቅሰው፥ ከነገ ጀምሮ በሚካሄደው መድረክ የሃይማኖት ተቋማት፣ የመገናኛ ብዙሃን፣የዴሞክራሲ ተቋማት፣የፖለቲካ ፓርቲዎችና የመንግስት ውክልና ያላቸው ተሳታፊዎች እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በቀጣይ ከትግራይ ክልልና ከዳያስፖራው አጀንዳ የማሰባሰብ ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ ባከናወናቸው ተግባራት ልዩነትና አለመግባባትን በንግግር ለመፍታትና አገራዊ አቅም ለመፍጠር የሚያስችሉ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።

የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራው ከተጠናቀቀ በኋላ አጀንዳ የመቅረፅ፣ ከሚመጡ አጀንዳዎች መካከል መሰረታዊና አገራዊ አጀንዳዎችን የመለየት፣ አገራዊ የምክክር ጉባኤ ማዘጋጀትና መግባባት የተደረሰባቸው ጉዳዮች ተፈፃሚ እንዲሆኑ ምክረ ሃሳብ አዘጋጅቶ ለፈጸሚ አካላት ማቅረብና ተፈፃሚነታቸውን መከታተል የኮሚሽኑ ሌሎች ተግባራት መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ሂደቱ ውጤታማ እንዲሆን፣በህዝቡና በሌሎች ባለድርሻ አካላት ያለውን ቅቡልነት ለማረጋገጥ የተግባቦት ስራም በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

አገራዊ ምክክር ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን በውይይት የመፍታት ባህልን የሚያዳብር በመሆኑ ለምክክሩ ስኬት ሁሉም የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም