የኤም ፖክስ ቫይረስን አስቀድሞ ለመከላከል በሁሉም ክልሎች ዝግጅት ተደርጓል -ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ - ኢዜአ አማርኛ
የኤም ፖክስ ቫይረስን አስቀድሞ ለመከላከል በሁሉም ክልሎች ዝግጅት ተደርጓል -ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 20/2017(ኢዜአ)፦ የኤም ፖክስ ቫይረስን አስቀድሞ ለመከላከል በሁሉም ክልሎች ዝግጅት መደረጉን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ አስታወቁ።
ሚኒስትሯ ቫይረሱን ለመከላከል በተከናወኑ ተግባራት ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም፥ የኤም ፖክስ ቫይረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ በ133 አገራት በአፍሪካ ደግሞ በ29 አገራት መከሰቱን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ በሞያሌ አካባቢ የሚኖር የ21 ቀን ህጻን በበሽታው መያዙ መለየቱን ጠቅሰው፤ በህጻኑ እናትና አባት ላይ በተደረገ የናሙና ምርመራ በሽታው እንዳለባቸው መረጋገጡን አመልክተዋል።
በበሽታው የተያዙት ሰዎች በለይቶ ማቆያ አስፈላጊው እንክብካቤ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸው፤ ታማሚዎቹ በጥሩ ጤንነት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ አላቸው የተባሉ አምስት ሰዎች ላይ ናሙና ተወስዶ ምርመራ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
ጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ጋር በመተባበር የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ማስተባበሪያና ምላሽ መስጫ ማዕከል በማቋቋም የመለየት እና የቅኝት ስራዎች እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በድንበር አካባቢ፣በአየርና በየብስ መውጫ እና መግቢያ በሮች የቁጥጥር ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉንም ተናግረዋል።
ከውጪ የሚገቡ ተጓዞች የጉዞ ታሪክ እንዲመዘገብ በማድረግ፣ በአጎራባች ቦታዎች እንዲሁም ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ የቁጥጥር ሥራው በስፋት እየተካሄደ ነው ብለዋል።
ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ያሉ ጤና ተቋማት የአገልግሎት አቅማቸው ከፍ እንዲል በህክምና ቁሳቁስና ግብዓት እንዲጠናከሩ እየተደረገ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎችም በሽታውን በተመለከተ ግንዛቤያቸው እንዲያድግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የፈጣን ምላሽ ቡድን በማቋቋም በተለያዩ ክልሎች የሚሰማራ መሆኑን ገልጸው፤በሁሉም ክልሎች በሽታውን አስቀድሞ የመከላከል ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም አንስተዋል።
ለበሽታው ከተጋለጠ ሰው ጋር ግንኙነት ያለው ሰው በአፋጣኝ ሪፖርት ማድረግ እንዳለበት ጠቅሰው፤ ሽፍታ፣ትኩሳት፣የንፍፊት እብጠት፣ የመገጣጠሚያ ህመም ምልክት የታየበት ሰው በአፋጣኝ ወደ ህክምና ቦታ በመሄድ መታከም እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ኀብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው፥ለበሽታው ከተጋለጠ ሰው ጋር ንክኪ መቀነስ፣ በሽታው የተከሰተባቸው አካባቢዎች የጉዞ ታሪክ ያላቸው ሰዎች እስከ 21 ቀን ራሳቸውን መለየት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ትልቅ ሚና እንዳለው አብራርተዋል።
እንደ ዶክተር መሳይ ገለጻ፤ በሽታው ሁሉንም ሊያጠቃ የሚችል ሲሆን፤ በተለይም ህጻናት፣ ነፍሰ ጡር እናቶች እና የበሽታ መለካከል አቅም በሚቀንሱ ተጓዳኝ ህመም የተያዙ ሰዎች ተጋላጭነታቸው ከፍ እንደሚልም አስረድተዋል።