ቀጥታ፡

በሀገራዊ ምክክሩ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ገንቢ ሚናችንን ማጠናከር አለብን-የሃይማኖት አባቶች

አዲስ አበባ፣ግንቦት 20/2017 (ኢዜአ)፦በሀገራዊ ምክክሩ ንቁ ተሳትፎ በማድረግና ገንቢ ሚናችንን ማጠናከር አለብን ሲሉ የሃይማኖት አባቶች ገለጹ።

ምክክር የህዝብን አብሮነት ለማጠናከርና ለመጪው ትውልድ የተሻለች ሀገር ለማስረከብ ሁነኛ መፍትሄ መሆኑንም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥና የህዝቦች አብሮነትን የበለጠ ለማጎልበት ችግሮችንና በመሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያሉ አለመግባባቶችን ለመፍታት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ እየሰራ ነው።

ኮሚሽኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር የውይይት አጀንዳ እየሰበሰበ የሚገኝ ሲሆን ለስራው ውጤታማነት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ ነው።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የተለያዩ የሃይማኖት አባቶች ሀገራዊ ምክክሩ በኢትዮጵያ አለመግባባቶችን በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ ለመፍታት ሁነኛ መፍትሄ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽህፈት ቤት የይግባኝ ሰሚ መንፈሳዊ ፍርድ ቤት መምሪያ ዳኛ ንቡረ-ዕድ አባ ዮሃንስ ገብረህይወት፣ ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት የህዝብ አብሮነት ጉልህ ሚና እንዳለው አስረድተዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በውይይትና በሰላማዊ ንግግር መፍታትም የሥልጣኔ ምልክትና የህዝብን አንድነት ለማጠናከር ቁልፍ መሳሪያ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት በኢትዮጵያ የሀሳብ ልዩነትን በምክክር በመፍታት ወደተሻለ ምዕራፍ ለመሻገር ታሪካዊ ዕድሎች በመሆናቸው በአግባቡ ልንጠቀምባቸው ይገባል ብለዋል።

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ ሼህ ሁሴን በሽር፥ የሀሳብ ልዩነት የጠብ መነሻ ከመሆኑ በፊት ሊያግባቡና ሊያስማሙ የሚችሉ ነገሮችን ማጉላት እንደሚገባ አንስተዋል።

የጋራ መግባባት መፍጠርም የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ ነው አጽንኦት የሰጡት።

በዚህ ረገድ ሀገራዊ ምክክሩ ለትውልዱ የተሻለ ሀገር ለመገንባትና የህዝቡን አብሮነት የበለጠ ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የሃይማኖት አባቶችም በምክክሩ ሂደት ገንቢ አስተዋፅኦን ማጠናከርና ትውልዱ የውይይትን ባህል፣ ይቅር ባይነትንና ትህትናን እንዲያጎለብት የማስተማር ሚናችንን ልናጎለብት ይገባል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ ቃለ ህይወት ቤተክርስቲያን አገልጋይ የሆኑት መጋቢ ደረጀ ካሳሁን፥ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማት ሚናው የጎላ በመሆኑ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኢትዮጵያ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ምክንያቶችን በጥናትና በህዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተመረጡ አጀንዳዎች ላይ ሀገራዊ ምክክሮችን በማካሄድ ለአገራዊ መግባባት ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ተልዕኮ ይዞ እየሰራ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም