ቤተክርስቲያኗ ለዘላቂ ሰላምና አንድነት የበለጠ መጠናከር በልዩ ትኩረት እንደምትሰራ ገለጸች - ኢዜአ አማርኛ
ቤተክርስቲያኗ ለዘላቂ ሰላምና አንድነት የበለጠ መጠናከር በልዩ ትኩረት እንደምትሰራ ገለጸች
አዲስ አበባ፤ግንቦት 20/2017(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለዘላቂ ሰላምና አንድነት የበለጠ መጠናከር በልዩ ትኩረት እንደምትሰራ ገለጸች።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ላለፉት ቀናት ሲያካሂድ በቆየው የግንቦት ርክበ ካህናት መደበኛ ጉባኤ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፋለች።
ቅዱስ ሲኖዶስ ከግንቦት 6 ቀን እስከ 19 ቀን 2017 ዓ.ም ሲያካሄድ የቆየውን የርክበ ካህናት መደበኛ ጉባኤ መጠናቀቁን ተከትሎ መግለጫ ሰጥቷል።
የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብጹዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ሲኖዱሱ በሰጠው መግለጫ በጉባኤው የተለያዩ ውሳኔዎችን ማሳለፉን ገልጸዋል።
ከኮሪደር ልማት ጋር በተያያዘ የቤተ ክርስቲያኗ ይዞታዎችን መልሶ በመገንባት እና ምትክ በመስጠት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ላደረጉት ትብብር ቅዱስ ሲኖዶስ ምስጋናውን አቅርቧል ብለዋል።
በውሳኔው ለሀገር ዘላቂ ሰላም ግንባታ የሚደረጉ ተግባራትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንዲሁም ስለሰላምና አብሮነት ዘወትር መጸለይና መስራት እንደሚገባ ጥሪ መደረጉን ገልጸዋል።
በተጨማሪም በሰላምና አንድነት ልዩ ትኩረት አድርጎ ሁሉን አቀፍ ስራ እንደሚሰራ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብጹዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ተናግረዋል።
አለመግባባቶችን በውይይት በመፍታት አብሮነትን ማጠናከር እንደሚገባ በርክበ ካህናት መደበኛ ጉባኤው አፅንኦት እንደተሰጠው አንስተዋል።
የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ሲሰሩ የነበሩ ብፁዓን አባቶች የሥራ ዘመናቸውን በማጠናቀቃቸው ለቀጣይ ሦስት ዓመታት የሚሠሩ ብፁዓን አባቶች መመረጣቸውን አስታውቀዋል።