ኢትዮጵያ ታራሚዎች ሰብዓዊ መብታቸው ተከብሮ የንቃተ ህግ አቅማቸው ዳብሮ ታርመውና ታንጸው ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ እየሰራች ነው - ኮሚሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ታራሚዎች ሰብዓዊ መብታቸው ተከብሮ የንቃተ ህግ አቅማቸው ዳብሮ ታርመውና ታንጸው ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ እየሰራች ነው - ኮሚሽኑ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 20/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ስታንዳርድ እና በሀገራዊ ህጎች መሰረት ታራሚዎች ሰብዓዊ መብታቸው ተከብሮ የንቃተ ህግ አቅማቸው ዳብሮ ታርመውና ታንጸው ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ እየሰራች መሆኑን የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽነር የኑስ ሙሉ ገለጹ።
19ኛው የፌዴራል እና የክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽነሮች የጋራ ጉባኤ "ማረሚያ ቤቶችን በአዲስ አስተሳሰብ ወደ አዲስ ምዕራፍ" በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ነው።
በመርሀ ግብሩ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት፣ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሌሊሴ ደሳለኝ፣ የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ዑመድ ኡጁሉ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ብርሀኑ አዴሎን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽነሮችና እንግዶች ተገኝተዋል።
የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽነር የኑስ ሙሉ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የሕግ ታራሚዎችን መሰረታዊ ፍላጎት ማሟላት ለማረምና ለማነፅ ስራችን ስኬታማነት የጎላ አበርክቶ አለው።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ስታንዳርድ እና በሀገራዊ ህጎች መሰረት የታራሚዎች ሰብዓዊ መብታቸው ተከብሮ የንቃተ ህግ አቅማቸው ዳብሮ ታርመውና ታንጸው ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።
ሰብዓዊ መብታቸው የተከበረ፣ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ወስደው በሥነ ምግባር የታነጹ፣ አምራችና ህግ አክባሪ ዜጎች እንዲሆኑ ተቋማዊ ሪፎርም ተደርጓል ነው ያሉት።
ሪፎርሙም በሰብዓዊ መብት አያያዝ አዎንታዊ ለውጥ አምጥቷል ብለዋል።
ማረሚያ ቤቶች የእርምት የልማትና የልህቀት ማዕከል እንዲሆኑ ለማድረግ በትጋት እየሰሩ መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ በዚህም የማረሚያ ቤቶች በሰብዓዊ ጥሰት የማይከሰሱበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል።
የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ ዑመድ ኡጁሉ በበኩላቸው፤ ባለፋት ሰባት ዓመታት በፍትህ ዘርፉ የተደረገው ሪፎርም ተጨባጭ ውጤት ማምጣቱን ገልጸዋል።
መንግስት ለፍትህ ዘርፉ ትኩረት በመስጠት ማረሚያ ቤቶች በፍርድ ቤት ውሳኔ ብቻ ታራሚዎችን እንዲቀበሉ ተደርጓል ብለዋል።
ታራሚዎች ዘመናዊ ትምህርትና ስልጠና ወስደው ህግ አክባሪና አስከባሪ ዜጎች እንዲሆኑ የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱንም ገልጸዋል።
ማረሚያ ቤቶች የታራሚዎችን ሕገ መንግስታዊ መብት በማክበር የማነፅ ስራቸውን ዘመኑን በዋጀ ቴክኖሎጂ ማዘመን አለባቸው ብለዋል።