ቀጥታ፡

በዩኒቨርሲቲው እየተገነቡ የሚገኙ ፕሮጀክቶች የግንባታ አፈጻጸም አበረታች ነው - ባለሥልጣኑ

ሮቤ፤ ግንቦት 20/2017(ኢዜአ)፦ በመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ እየተገነቡ የሚገኙ ፕሮጀክቶች የግንባታ አፈጻጸም አበረታች መሆኑን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን አመለከተ። 

የባለስልጣኑ አመራሮች እና ባለሙያዎች በዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ካምፓሶች እየተገነቡ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን የሚገመግም የሰነድና የመስክ ምልከታ አካሂደዋል። 

የባለሥልጣኑ የቁጥጥር ቡድን ከተመለከታቸው የዩኒቨርሲቲው ፕሮጀክቶች መካከል ባለ ስምንት ወለል የማስተማሪያና የህክምና ሪፈራል ሆስፒታል ህንጻ ግንባታ፣ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ፣ ቤተ መጻህፍትና ቤተ-ሙከራዎች ይገኙበታል። 

በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ግንባታ ቁጥጥር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር በረከት ተዘራ እንዳሉት ተቋሙ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች በጥራትና በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ እያከናወነ ይገኛል። 


 

መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲም ባለሥልጣኑ የቁጥጥር ሥራ ከሚያደርግባቸው የመንግሥት ተቋማት አንዱ መሆኑን ጠቁመው በዩኒቨርሲቲው እየተገነቡ የሚገኙ ፕሮጀክቶችም በጥሩ ሂደት ላይ መሆናቸውን ባካሄዱት የሰነድና የመስክ ምልከታ ግምገማ ማስተዋላቸውን ተናግረዋል። 

በተለይ የግንባታ ሂደቱ ወደ መጠናቀቅ የተቃረበው ባለ ስምንት ወለል የጎባ ሪፈራል ሆስፒታል ህንጻ ግንባታ አፈጻጸምና ጥራት ከሌሎቹ የተለየ መሆኑን አስታውሰዋል። 


 

በዩኒቨርስቲው በመንግሥት በጀት የሚገነቡ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ከሚደረገው ክትትል በተጓዳኝ የግንባታ ሥራዎቹ የአካባቢንና የማህበረሰብን ደህንነት ባማከለ መልኩ ስለመከናወናቸው እንደሚታይም አስረድተዋል። 

በመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በሰነድ የቀረበው ሪፖርትና በመስክ ምልከታው በመሬት ላይ ያለው የግንባታ አፈጻጸም ደረጃ ተቀራራቢና በመልካም ተሞክሮነቱ ለሌሎች ተመሳሳይ ተቋማት ልምድ የሚሆን ነው ብለዋል። 

ፕሮጀክቶቹ በጥራት ተገንብተው በተያዘላቸው ጊዜ መጠናቀቅ ባለስልጣኑ የሚያደርገውን ክትትል፣ ድጋፍና ቁጥጥር  አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ኢንጂነር በረከት አረጋግጠዋል። 


 

የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አህመድ ከሊል(ዶ/ር) በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው እየተከናወኑ የሚገኙ የግንባታ ፕሮጀክቶች ተቋሙ እያካሄደ ለሚገኘው የመማር ማስተማር፣ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ተግባራት አጋዥ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

ፕሮጀክቶቹ በፍጥነት እና በጥራት ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ በየደረጃው የሚገኙ የዘርፉ ባለሙያዎችና አመራሮች ርብርብ እያደረጉ መሆኑንም አስረድተዋል። 

የባለስልጣኑ አመራሮችና ባለሙያዎች የመስክ ምልከታና ግብረ-መልስ በዘርፉ የሚታዩ መልካም አጋጣሚዎችን ለማጠናከርና በሥራ ሂደት ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እንዲፈቱ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ጨምረው ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም