ቀጥታ፡

በክልሉ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሕብረተሰቡ የድጋፍ ተሳትፎ ተጠናክሮ ቀጥሏል

ባህር ዳር፤ ግንቦት 20/2017(ኢዜአ)፡-  በአማራ ክልል በበጀት ዓመቱ ያለፉት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ የሚውል 89 ሚሊዮን ብር  ሃብት ከሕብረተሰቡ ማሰባሰብ እንደተቻለ የክልሉ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎና ድጋፍ አሰባሳቢ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መጋቢት 11/2017ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕዳሴ ግድብን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ እየተገባደደ የሚገኘው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ  ኢትዮጵያ መቻልን ያሳየችበት እንደሆነ መግለጻቸው ይታወሳል።


 

የሕዳሴው ግድብ የመሰረተ ድንጋይ ከተቀመጠበት ጊዜ አንስቶ የአማራ ክልል ሕዝብ እንደሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ድጋፉን  አጠናክሮ መቀጠሉን ጽሕፈት ቤቱ ገልጿል። 

የጽሕፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ አባይነህ ጌጡ፤ የክልሉ ህዝብ ለሕዳሴ ግድቡ ግንባታ ስኬታማነት በከፍተኛ ተነሳሽነት ድጋፋን እያደረገ እንደሚገኝ ለኢዜአ ተናግረዋል። 

የሕብረተሰቡን ያልተቋረጠ ድጋፍ አጠናክሮ በማስቀጠልም በበጀት ዓመቱ ከ100 ሚሊዮን ብር ያላነሰ ገቢ ለመሰብሰብ ግብ ተይዞ ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመው በዚህም እስከ ሚያዚያ 30/2017 ዓ.ም በተደረገ የተቀናጀ ጥረት 89 ሚሊዮን ብር ማሳካት ተችሏል ነው ያሉት።

የተሰበሰበው ገቢም ከባለፈው ሙሉ ዓመት ጋር ሲነፃፀር ከእጥፋ በላይ ብልጫ እንዳለው አስታውቀዋል። 

በጥሬ ገንዘብ ከተሰበሰበው በተጨማሪ ሕብረተሰቡ ከ170 ሚሊዮን 590 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በማከናወን ግድቡን ከደለል ለመጠበቅ የሚያግዝ ስራ ማከናወን እንደተቻለ አብራርተዋል።

ችግሮችን በመቋቋም ክልሉ ለፕሮጀክቱ ድጋፉንና ቁርጠኝነቱን በተግባር ማሳየቱን አጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

የክልሉ ሕዝብ የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ አንስቶ ድጋፉን በጥሬ ገንዘብ እና የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ ላይ በንቃት በመሳተፍ ማገዙን ጽህፈት ቤቱ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም