ቀጥታ፡

የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን ከሲዳማ ቡና ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ይጠበቃል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 20/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ32ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳል።

የዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ በሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን እና ሲዳማ ቡና መካከል ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይደረጋል።

ኢትዮጵያ መድን በ60 ነጥብ የሊጉ አናት ላይ ሲቀመጥ ሲዳማ ቡና በ46 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ኢትዮጵያ መድን ካሸነፈ ከተከታዩ ኢትዮጵያ ቡና ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ዘጠኝ ከፍ ያደርጋል።

ባለፉት ስምንት የሊጉ ጨዋታዎች ሽንፈት ያላስተናገደው ሲዳማ ቡና ካሸነፈ በድል ጉዞው እንዲቀጥል ያደርገዋል።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ምሽት 12 ላይ ባህር ዳር ከተማ ከአርባምንጭ ከተማ ይጫወታሉ።

ባህር ዳር ከተማ በ48 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ አርባምንጭ ከተማ በ36 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ባለፉት ሶስት የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ ያልቻለው ባህር ዳር ከተማ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ወደ ድል እንዲመለስ ያደርገዋል።

በሊጉ ካሸነፈ ሁለት ወራት ያስቆጠረው አርባምንጭ ከተማ ድሉን ለመነሳሻነት ለመጠቀም ያስችለዋል።

የ32ኛ ሳምንት መርሃ ግብር እስከ ግንቦት 23 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም