የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት ላይ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ማጠናከር አለበት -የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት ላይ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ማጠናከር አለበት -የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
አዲስ አበባ፤ግንቦት 19/2017(ኢዜአ)፦ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት ላይ እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባራትን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።
የኢትዮጵያን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ፋላጎት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ምላሽ የሚሰጥ አቅም መፈጠሩን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 32ኛ መደበኛ ስብሰባ አባላቱ ለውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ምላሽና ማብራሪያ የሚሹ አስተያየትና ጥያቄዎችን አቅርበዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)÷ የዜጎችን የንጹህ መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት፣ የሃይቅና ወንዞችን ውሃ አካላትን ደኅንነት ለመጠበቅ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በዚህም በተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር ሥርዓት የኢትዮጵያን የከርሰ ምድርና የገጸ ምድር የውሃ አለኝታ በዘመናዊ መረጃ በማደራጀት ስኬታማ ስራ መስራት እንደተቻለ ገልጸዋል።
ለአብነትም የገጸምድር ውሃ ሃብት አለኝታን ከነበረበት 83 ነጥብ 7 በመቶ በበጀት ዓመቱ በዘጠኝ ወራት ወደ 85 በመቶ ማድረስ እንደተቻለ አስታውቀዋል።
የምክር ቤቱ አባላትም ሚኒስቴሩ የኢትዮጵያን የከርሰ ምድርና የገጸ ምድር የውሃ ሃብት በብዛትና ጥራት በማዘመን የዜጎችን የውሃ አቅርቦትና ተደራሽነት ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት የሚደረጉ ጥረቶችን አድንቀዋል።
የከተማና ገጠር የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ የሃይቆችና ወንዞች ደኅንነት ጥበቃ፣ የውሃ መሰረተ ልማት፣ የፕሮጀክት ግንባታና የኢትዮጵያን የውሃ ሽፋን ዕድገት ላይ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን ጠይቀዋል።
በሀገሪቱ ለድርቅ ተጋላጭ የሆኑና የከርሰ ምድር ውሃ በሌለባቸው አካባቢዎች ለሚኖሩ ዜጎች አማራጭ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ልማት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ 17 ሚሊየን ዜጎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል።
በቀጣይም የፕሮጀክቶችን የመፈጸም አቅም በማሳደግ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ፍላጎትን ምላሽ በመስጠት፤ የሃይቆችና ወንዞችን ደህንነት የመጠበቅ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በፌደራል መንግስት ከሚገነቡ የውሃ ፕሮጀክቶች በተጨማሪም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮችን መተጋገዝ የሚችሉበት አቅም እንዲፈጥሩ የምክር ቤቱ አባላት ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩም ጠይቀዋል።
በአጠቃላይ እ.አ.አ. በ2030 የኢትዮጵያ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት መቶ በመቶ ለማድረስ በተቀመጠው ዕቅድ መሰረት ማሳካት የሚያስችል የማስፈጸም አቅም መፈጠሩን አስታውቀዋል።
ምክር ቤቱ በ32ኛ መደበኛ ስብሰባው የሥርዓተ ምህዳር አገልግሎት ክፍያ ረቂቅ አዋጅና የባለብዙ ተዋንያን የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል።