በሞያሌ ከተማ በሁለት ሰዎች ላይ የተገኘው ኤም ፖክስ በሽታ እንዳይዛመት የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው - ቢሮው - ኢዜአ አማርኛ
በሞያሌ ከተማ በሁለት ሰዎች ላይ የተገኘው ኤም ፖክስ በሽታ እንዳይዛመት የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው - ቢሮው
ግንቦት 19/2017(ኢዜአ)፦ በሞያሌ ከተማ በሁለት ሰዎች ላይ የተገኘው ኤም ፖክስ በሽታ እንዳይዛመት የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ።
የቫይረሱን መከሰት ተከትሎ የጤና ሚኒስቴር ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተጠናከረ ጥረት የሚደረግ መሆኑን በመግለጽ ህብረተሰቡም የሚወጡ መረጃዎችን በአግባቡ በመከታተል ራሱንና ቤተሰቡን ከበሽታው ለመጠበቅ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ማሳሰቡ ይታወቃል።
ኤም ፖክስ(Mpox) በሽታ በዝንጀሮ በ'ጂነስ ኦርቶፖክስ ቫይረስ' የሚመጣ ተላላፊ በሽታ ሲሆን በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር በአካል ንክኪ ወይም በበሽታው ከተያዙ እንስሳት ወደ ሰው ሊተላለፍ እና በወረርሽኝ መልክ ሊከሰት እንደሚችል ተመላክቷል፡፡
የበሽታው ምልክቶችም ሽፍታ፣ ሳል፣ ትኩሳት፣ የራስ ምታት፣ የእጢ እብጠት፣ የቆዳ ቁስለትና ድካም፣ የጡንቻ እና የጀርባ ህመም ሊኖረው እንደሚችል የጤና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ሞያሌ ከተማ አስተዳደር በበሽታው ከተጠረጠሩ ሰዎች በተወሰደ ናሙና በሁለት ሰዎች ላይ በሽታው እንደተገኘ አሳውቋል።
ቫይረሱ የተገኘባቸውም የ21 ቀን እድሜ ባለው ህጻን እና እናቱ ላይ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን አስቀድሞ በተዘጋጀ የለይቶ ማቆያ ተገቢ የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ሚኒስቴሩ መግለጹ ይታወሳል።
በመሆኑም በሽታው በአካባቢው እንዳይዛመት የመከላከልና በማህበረሰቡ ዘንድ ግንዛቤ ከመፍጠር አንፃር ምን እየተሰራ እንደሆነ ኢዜአ የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮን አነጋግሯል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ተስፋዬ ከበበው፤ በከተማ አስተዳደሩ እና አካባቢው የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ልዩ ተልዕኮ በመውሰድ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ቫይረሱ የተገኘባቸው እናት እና ህጻን ልጇ በአካባቢው በሚገኝ የጤና ተቋም ተለይተው የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቁመው፤ ተገቢው የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
የቫይረሱ ስርጭት እንዳይኖር በአካባቢው በከፍተኛ ጥንቃቄ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ገልጸው እስካሁን ከሁለቱ ሰዎች ውጪ ሌላ ታማሚ አለመኖሩን አረጋግጠዋል።
በሽታው መከሰቱ ከተረጋገጠ ጊዜ ጀምሮ የክልሉ ጤና ቢሮ የሚመለከታቸውን አካላት በማስተባበር ግብረ ሃይል አቋቁሞ በተጠናከረ መልኩ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በከተማ አስተዳደሩ ያሉ የጤና ባለሙያዎች በበሽታው ዙሪያ ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማሳደጊያ ስራዎችን በስፋት እያከናወኑ መሆኑን ዶክተር ተስፋዬ ተናግረዋል።
የበሽታውን ምልክቶች፣ የመተላለፊያና መከላከያ መንገዶቹንና ተያያዥ ሁኔታዎችን በተመለከተ ለማህበረሰቡ ተከታታይ የግንዛቤ ማሳደጊያ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።
በዚህም ህብረተሰቡ ተገቢውን ግንዛቤ በማግኘት ጥንቃቄ እያደረገ መሆኑን ገልጸው አሁን ባለው ሁኔታ ስርጭቱን በሚመለከት የሚያሰጋ ነገር እንደሌለም ተናግረዋል።
በመሆኑም የከተማውም ሆነ የአካባቢው ማህበረሰብ እያደረገ ያለው ጥንቃቄ እንዳለ ሆኖ መደበኛ የስራ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚችሉ ገልጸዋል።
በዚህ አጋጣሚ የበሽታው ምልክት የታየበት ማንኛውም ግለሰብ በአቅራቢያው ወደሚገኝ ጤና ተቋም ፈጥኖ በመሄድ አስፈላጊውን የህክምና ክትትል ማግኘት ይኖርበታል ሲሉም አሳስበዋል።
የኤም ፖክስ ቫይረስ በዴንማርክ እ.ኤ.አ በ1958 ዓ.ም በዝንጀሮዎች ላይ የተገኘ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ በሰው ልጅ ላይ የታየው ደግሞ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ጤና ሚኒስቴር በሽታው በአፍሪካ መከሰቱ ከታወቀ ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ እና ከገባም መቆጣጠር የሚያስችል ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱም ታውቋል።