ቀጥታ፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት ትብብርና ቅንጅት ለዜጎች ተጠቃሚነት ጉልህ ፋይዳ አለው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 18/2017(ኢዜአ)፦የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት ትብብርና ቅንጅት ማድረግ ለዜጎች ተጠቃሚነት ጉልህ ፋይዳ እንዳለው በዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ሚኒስትር አቶ መለሰ ዓለሙ ገለጹ።       

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና ባለድርሻ አካላት ትብብርና ቅንጅት መድረክ አካል የሆነው የፌዴራልና የክልሎች አመራር አባላት ፎረም ተካሂዷል።   


 

በፎረሙ ላይ የክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች የዲሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊዎች፣ የክልል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ጥምረቶችና ተወካዮች፣ የፌዴራል ትብብርና ቅንጅት መድረክ ዐቢይና ንዑስ ኮሚቴ አባላት ተገኝተዋል።  

በዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ሚኒስትር አቶ መለሰ ዓለሙ እንዳሉት፤ ልማት፣ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እንዲሁም ዘላቂ ልማት እንዲሳካ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተሳትፎ ወሳኝ ሚና ይጫወታል።  

ለዚህም ጠንካራ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን መፍጠር ቀዳሚ አጀንዳ ሊሆን ይገባል ያሉት ሚኒስትሩ፤ መንግሥትም ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ማጠናከር ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አመልክተዋል።  

ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚያበረክቱትን አገራዊ አስተዋጽኦ ለማሳደግም በፌዴራል ደረጃ የቅንጅትና ትብብር መድረክ መመስረቱን ጠቁመው፤ ተግባሩ ክልሎችን ጨምሮ ወደታችኛው መዋቅር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስረድተዋል። 


 

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ በበኩላቸው፤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ተሳትፎ ለማጎልበት የተከናወኑ የለውጥ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤቶች እያመጡ መሆኑን ተናግረዋል።      

በዛሬው የውይይት መድረክም ባለድርሻ አካላትና ክልሎች በታችኛው መዋቅር የሚኖራቸውን እንቅስቃሴ ለማሳደግ የጋራ ግንዛቤ እንዲሁም መግባባት ላይ ለመድረስ ያለመ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ አህመድ ሁሴን እንደገለጹት፤ የቅንጅትና የትብብር መድረኩ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በተመለከተ የወጡ አዋጆች በአግባቡ እንዲተገበሩ አወንታዊ ሚና ይጫወታል።       

በባለድርሻ አካላትና በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መካከል ከዚህ ቀደም በነበሩ የቅንጅት ክፍተቶች ሳቢያ የታጡ ዕድሎች ለማካካስ መሥራት ሌላው የመድረኩ ዓላማ መሆኑም ጠቅሰዋል።  

ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በትምህርት፣ ግብርናና ሌሎች ዘርፎችም የፖለሲ አማራጭ እንዲያቀርቡ የትብብርና የቅንጅት መድረኩ አስቻይ ሁኔታ እንደሚፈጥር አብራርተዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በበኩላቸው፤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት የትብብርና ቅንጅት መመሪያን የያዘ ሰነድ አቅርበዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ሥልጠና በመስጠት አቅም መገንባትና የፋይናንስ ምንጫቸው እንዲጎለብት መደገፍ መመሪያው ከያዛቸው ጉዳዮች መካከል መሆኑን ጠቅሰዋል።   

አገር በቀል ድርጅቶችን ማጠናከርና መሰረታቸው እንዲሰፋ በማድረግ ለአገር የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ እንዲጨምር ማድረግ እንዲሁ የመመሪያው አካል መሆኑን ገልጸዋል።

ከፎረሙ ተሳታፊዎች መካከል የሲዳማ ክልል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ማስረሻ ክብረት እንዳሉት፤  በክልል ደረጃ የትብብርና የቅንጅት መድረኩን በሙሉ አቅም ወደ ሥራ ለማስገባት ርብርብ እየተደረገ ነው።  

ከአማራ ክልል የተወከሉትና የህብረት ለትብብርና ልማት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጋቱ ደስታ በበኩላቸው፤ መድረኩ ለዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እውን መሆን ሚናችንን እንድንወጣ አጋዥ ነው፤ የሚጠበቅብንን ለመወጣት ዝግጁ ነን ብለዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት ተቀራርቦ መሥራት ውጤቱ ከፍ ያለ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ያሉት ደግሞ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ተወካይ አቶ አክሊሉ መኔዶ ናቸው።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም