በአማራ ክልል የሲቪል ሰርቪስ ተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥን የማሻሻል ስራ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የሲቪል ሰርቪስ ተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥን የማሻሻል ስራ እየተከናወነ ነው
ደብረብርሃን፤ ግንቦት 18/2017(ኢዜአ)፦በአማራ ክልል የሲቪል ሰርቪስ ተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥን የማሻሻል ስራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ኮሚሽነር ባንቺ አምላክ ገብረሚካኤል ገለጹ።
በክልሉ የመንግስት ሰራተኞች የትምህርት ማስረጃ የማጣራት ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ኮሚሽነሯ አስታውቀዋል።
በደብረብርሃን ከተማ ከዞኖች ከተወጣጡ የመምሪያ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር በተካሔደው የ10 ወራት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ ላይ ኮሚሽነሯ እንደገለጹት የክልሉን የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል በትኩረት እየተሰራ ነው።
በበጀት ዓመቱ አዲሱን የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርምና አደረጃጀት ተግባራዊ የማድረግ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በሂደቱም የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው በተለይም የሰራተኞችን የትምህርት ማስረጃ የማጣራት ስራ በልዩ ጥንቃቄ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
የሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃን ለማጣራት በተደረገ ጥረት እስከ አሁን የ18 ሺህ ሰራተኞች ማስረጃ በሶፍት ኮፒ ደርሶናል ሲሉም ተናግረዋል።
በመሆኑም የሲቪል ሰርቪሱን አገልግሎት ቀልጣፋና ዘመናዊ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ከምንም በላይ የሰው ኃይል ብቃትን ማረጋገጥና የቴክኖሎጂ አቅምን ማሳደግ ይገባል ብለዋል።
የሀሰተኛ ትምህርት ማስረጃ የማጣራቱ ተግባር ሀገራዊ ኃላፊነትን በእውነትና በእውቀት በመታገዝ በቁርጠኝነት ለመወጣት መሆኑን አንስተው ይህም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።