ቀጥታ፡

13ኛው ከ20 ዓመት በታች የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በድሬዳዋ ተጀመረ

ድሬደዋ፣ግንቦት 18/2017(ኢዜአ)፦ከ1 ሺህ 190 በላይ ተተኪ ወጣቶች የተሳተፉበት 13ኛው ከ20 ዓመት በታች እና 4ኛው ከ18 ዓመት በታች የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ በድሬዳዋ ተጀምሯል።

በድሬዳዋ ዓለምአቀፍ ስታዲየም ዛሬ በተጀመረው በ13ኛው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች እና 4ኛው ከ18 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ከ1 ሺህ 190 በላይ ተተኪ ወጣት አትሌቶች ተሳትፈዋል።

በመክፈቻው ውድድር ላይ ከ20 ዓመት በታች የሶስት ሺህ ሜትር መሰናክል የሴቶች ሩጫ፣ ከ20 ዓመት በታች የወንዶች የከፍታ ዝላይ እና ከ20 ዓመት በታች የሴቶች የጦር ውርወራ የፍፃሜ ውድድሮች ተካሂደዋል።

በተጨማሪም በድሬደዋ ጎሮና ቡቱጂ እንዲሁም በማሪያም ሰፈር ትምህርት ቤቶች የሚሰለጥኑ ተተኪ ታዳጊ ህፃናት የተካፈሉበት የ800 ሜትር የሩጫ ውድድር ተካሄዷል።

በውድድሩ አሸናፊ ለሆኑት ህፃናት አትሌቶች የተዘጋጀውን ሜዳሊያዎች እና ሽልማቶች የሰጡት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አትሌት ኮማንደር ስለሺ ስህን ናቸው።

ኮማንደር አትሌት ስለሺ በወቅቱ ለኢዜአ እንደተናገሩት፥በየዕድሜ እርከኑ ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።

ተተኪዎች የሚፈሩበት ማሰልጠኛ ተቋማትን በተለያዩ አካባቢዎች ከመገንባት በዘለለ በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተተኪ ህፃናት አትሌቶችን የማፍራት ስራ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በድሬዳዋ ትምህርት ቤቶች በመሰልጠን ላይ የሚገኙትና ዛሬ በተጀመረው ሻምፒዮና ላይ የተሳተፉት ህፃናት የዚሁ ጥረት ማሳያ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ዛሬ የተጀመረው አገር አቀፍ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና አገርን በዓለም አደባባይ የሚያስጠሩ ተተኪዎችን የማፍራት ሂደት በመልካም ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

በድሬደዋ ዛሬ ከተጀመረው ሻምፒዮና የሚመረጡ አትሌቶች በሐምሌ ወር 2017 ዓ/ም በናይጄሪያ በሚካሄደው አህጉር አቀፍ ውድድር ላይ እንደሚሳተፉም ተናግረዋል።

የዕድሜ ጉዳይ የውድድሩ ችግር መሆኑን አንስተው፥ የተወዳዳሪ አትሌቶች ዕድሜም በዘመናዊ የህክምና መሳሪያ 'ኤም አር አይ' ተረጋግጦ የሚያልፉ መሆኑንም አመልክተዋል።

ውድድሩ እስከ ግንቦት 24 ቀን 2017ዓ.ም እንደሚቆይም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም