ቀጥታ፡

ባለፉት ዓመታት ቅርሶችን በማልማትና በማስተዋወቅ በተከናወኑ ተግባራት የቅርሶችን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ማሳደግ ተችሏል - ባለስልጣኑ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 17/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት ዓመታት ቅርሶችን በማልማትና በማስተዋወቅ በተከናወኑ ተግባራት ኢኮኖሚያዊ አስተዋጿቸውን ማሳደግ መቻሉን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ትኩረት ከተሰጣቸው የኢኮኖሚ መስኮች መካከል የቱሪዝም ልማት አንዱ ሲሆን ዘርፉን ለማሳደግ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል የቅርስ ልማት ስራ ተጠቃሽ ነው።

ከዚሁ ጎን ለጎን በሕገ-ወጥ መንገድ ከሀገር የወጡ በርካታ ቅርሶችን ማስመለስ ተችሏል። 

የባለስልጣኑ የቅርስ ምርምር መሪ ስራ አስፈፃሚ ዮናስ ይልማ(ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በቋሚ፣ በማይዳሰሱና በተንቀሳቃሽ ቅርሶች እምቅ ሃብት አላት።

በአሁኑ ወቅት ቅርሶችን በማልማት ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ያላቸውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የኢትዮጵያን የቅርስ ሃብቶች ከማልማት፣ ከመጠገንና ከማስተዋወቅ አንጻር ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

በሀገሪቱ አሁንም ያልታወቁና ለእይታ ያልበቁ ቅርሶች ላይ ጥናት በማድረግ በአለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅና ለጎብኚዎች ክፍት ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በቅርሶች ላይ የሚደረገውን ጥናትና ምርምር በማጠናከር እንዲሁም አልምቶ በመጠቀም ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸውን ይበልጥ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።


 

በኢትዮጵያ የብሔራዊ የቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ እና የቅርስ ባላደራ የቦርድ አባል አሉላ ፓንክረስት(ዶ/ር)፤ በኩላቸው በሕገወጥ መንገድ የወጡ የኢትዮጵያ ቅርሶችን ለማስመለስ የተጠናከረ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።  

በአሁኑ ወቅትም ቅርሶችን የማጥናት፣ የመመዝገብና የመጠገን ስራዎችን በልዩ ትኩረት በማከናወን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የማሳደግ ስራ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

አክለውም ወጣቱ ትውልድ ታሪኩን እንዲገነዘብና እንዲመራመር ማድረግ እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም