ሀገር አቀፍ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ነገ በድሬዳዋ መካሄድ ይጀምራል - ኢዜአ አማርኛ
ሀገር አቀፍ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ነገ በድሬዳዋ መካሄድ ይጀምራል
ድሬዳዋ፤ ግንቦት 17/2017(ኢዜአ)፦ ከ1ሺህ 190 በላይ አትሌቶች የሚሳተፉበት ሀገር አቀፍ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ነገ በድሬዳዋ እንደሚጀመር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።
የፌዴሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት ከፍተኛ ባለሙያ መሃሪ ነጋሽ እንደገለጹት፣ 13ኛው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች እና 4ኛው ከ18 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ነገ በድሬዳዋ ዓለም አቀፍ ስታዲየም በድምቀት ይጀመራል።
በውድድሩ በሁለቱም ጾታዎች ከክልሎች፣ ከአዲስ አበባ እና ከድሬዳዋ ከተሞች የተውጣጡ ከ1ሺህ 190 በላይ ወጣትና ተተኪ አትሌቶች በተለያዩ የአትሌቲክስ ስፖርቶች ይሳተፋሉ።
ውድድሩ በቀጣይ በናይጄሪያ ለሚካሄደው የአፍሪካ ከ18 ዓመት እና ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን የሚወክሉ ተተኪ አትሌቶችን ለመመልመል የሚያስችል ነው ብለዋል።
ውድድሩ ከነገ ጀምሮ ለሰባት ተከታታይ ቀናት በድሬዳዋ ዓለም አቀፍ ስታዲየም እንደሚካሄድም አስታውቀዋል።
የድሬዳዋ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አህመድ አብዶ በበኩላቸው ሻምፒዮናው በተሳካ መልኩ እንዲካሄድ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
ሻምፒዮናው ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች ለማፍራት ካለው ፋይዳ ባሻገር ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ ወጣቶች የእርስ በርስ ትስስርና አንድነታቸውን የሚያጠናክሩበት መሆኑንም ተናግረዋል።
በውድድሩ የሚሳተፉ ወጣት አትሌቶች በየውድድሩ ከአበረታች መድኃኒት ነፃ መሆናቸው እንደሚመረመር የገለጹት ደግሞ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ኮሚቴ አባል አትሌት አሸብር ደምሴ ናቸው።