በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ዝግጅት መርሃ ግብር የስራ ዕድል ተጠቃሚ ሆነናል - ተሳታፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ዝግጅት መርሃ ግብር የስራ ዕድል ተጠቃሚ ሆነናል - ተሳታፊዎች
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 17/2017(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ከተማ ለዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር የችግኝ ዝግጅት በተፈጠረላቸው የስራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ በችግኝ ዝግጅቱ እየተሳተፉ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ተናገሩ።
የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር የሀገሪቱን የደን ሽፋን ከማሳደግ ባለፈ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት ሰፊ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
በመርኃ-ግብሩ ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር አስተዋጽኦ እያበረከተ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ችግኝ የማፍላት ተግባር አንዱ ነው።
በአዲስ አበባ የካ እና ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተሞች ችግኝ በማፍላት ስራ ላይ የተሰማሩ ዜጎች ለኢዜአ እንዳሉት፤ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የስራእድል ተጠቃሚ ሆነዋል።
በመርሃ ግብሩ በተፈጠረው የስራ ዕድል ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ወይዘሮ ራሄል ዮሐንስ አንዷ ሲሆኑ በአሁኑ ወቅት ለቀጣይ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ የሚውሉ የተለያዩ ዝርያ ያላቸው ችግኞችን እያዘጋጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ከስራቸው በሚያገኙት ገቢ የቤተሰባቸውን ኑሮ ለማሻሻል እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።
ሌላዋ የስራ ዕድሉ ተጠቃሚ ሙሪዳ ዘይኒ እንዳሉት በችግኝ ማፍላት ተግባር ከስራ አጥነት ተላቀው በየእለቱ በሚሰሩት ስራ ቋሚ ገቢ እንዲኖራቸው እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።
በዚህም ቤተሰባቸውን በአግባቡ ለማስተዳደር እያገዛቸው መሆኑንም ነው ጨምረው ያነሱት።
የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ዝግጅት ስራ ለሀገር ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ላለው ልማት የበኩሉን ከመወጣት ባለፈ በግሉ ተጠቃሚ እንዳደረገው የሚናገረው ደግሞ አቶ ሙሉጌታ በዳዳ ነው።
በችግኝ ዝግጅት ሰራው ላይ በሚያደርገው ተሳትፎ ኑሮውን እያሻሻለ መሆኑን ተናግሯል።
በአዲስ አበባ ከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ የአረንጓዴ ቦታዎች አያያዝ ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክተር ሲሳይ አጥናፉ በበኩላቸው በመዲናዋ በመጪው ክረምት ለከተማ ውበትና ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞችን የማዘጋጀት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በዘንድሮው አመት በአስራ አንድ የችግኝ ጣቢያዎች እየተከናወነ ባለው የችግኝ ዝግጅትም ከ450 በላይ ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ጠቁመዋል።