የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽንን በቴክኖሎጂ የማደራጀት ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽንን በቴክኖሎጂ የማደራጀት ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 17/2017(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽንን በሰው ሃይልና ዘመኑ በሚጠይቀው ቴክኖሎጂ የማደራጀት ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የእሳትና አደጋ ሰራተኞች ቀን "ከአደጋ ስጋት ለተጠበቀ ከተማ ልማት የሚከፈል መስዋዕትነት ጀግንነት ነው" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ከተማ መስቀል አደባባይ እየተከበረ ይገኛል።
በመርሃ ግብሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ቡዜና አልከደር፣ የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚህ ወቅት የእሳትና አደጋ ሰራተኞች አደጋ በሚከሰትበት ወቅት የሰውን ህይወትና ንብረት የሚታደጉ ጀግኖች ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።
የቀኑ መከበር የእሳትና አደጋ ሰራተኞች ለሚሰጡት አገልግሎት አክብሮት ለመስጠትና ለማመስገን ነውም ብለዋል።
የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽንን በሰው ሃይልና ዘመኑ በሚጠይቀው ቴክኖሎጂ ተደራጅቶ ከተማውን የሚመጥን ስራ ማከናወን የሚያስችሉ ተግባራት መሰራታቸውን ጠቅስዋል።
ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ከንቲባ አዳነች ያረጋገጡት።
አዲስ አበባ ከተማን ለማዘመንና መሰረተ ልማትን ለማሟላት እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት የእሳት አደጋን በመከላከል በኩልም ጠቀሜታቸው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
በመርሃ ግብሩ ለእሳትና አደጋ ሰራተኞች የማዕረግ ማልበስ ስነ-ስርዓትና ዘመኑን የዋጁ የእሳትና አደጋ መከላከል ተሽከርካሪዎች ትርኢት ቀርቧል።