ቀጥታ፡

ብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት ወጣቱ በሀገርና ዘላቂ ሰላም ግንባታ ላይ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ እያስቻለ ነው - ሰላም ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 17/2017(ኢዜአ)፦ ብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት ወጣቱ በሀገርና ዘላቂ ሰላም ግንባታ ላይ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ እያስቻለ መሆኑን የሰላም ሚኒስቴር ገለፀ።

13ኛው ዙር የብሔራዊ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ስልጠና በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚሰጥ ተገልጿል።

በሰላም ሚኒስቴር አስተባባሪነት ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ እየተተገበረ ያለው የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት በዜጎች መካከል ማኅበራዊ ትስስርን መፍጠር እንዲሁም ብሔራዊ መግባባት፣ ዘላቂ ሰላምና ሀገር ግንባታን ለማጠናከር ያለመ ነው።

በሚኒስቴሩ የብሔራዊ በጎ ፈቃድ አገልግሎት መሪ ስራ አስፈፃሚ ገመቺሳ ኢቲቻ ለኢዜአ እንዳሉት መርሃ ግብሩ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ከ80ሺህ በላይ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶችን በማሰልጠን በሁሉም ክልሎች ማሰማራት ተችሏል።

በዚህም ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ወጣቶች ለአንድ ወር የተለያዩ ሥልጠናዎችን ተከታትለው ለስድስት ወራት ካደጉበት አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ በመሰማራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮም በ13ኛው ዙር አምስት ሺህ ወጣቶችን በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ማሰልጠን እንደሚጀመር ገልጸው፤ ወጣቶቹም ወደ ስልጠና ማዕከላቱ እየገቡ መሆኑን ነው የጠቀሱት።

መርሃ ግብሩ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የተለያዩ ቋንቋዎችን፣ ባህልና አኗኗር ዘይቤን እንዲገነዘቡ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

ወጣቱ ያለውን እምቅ አቅምና ችሎታ በመረዳት ብሎም ክህሎቱን እንዲያጎለብት ያስቻለ መሆኑን ገልጸው፤ የራሱ ስራ በመፍጠር እንዲሰራ እድል ያመቻቸ መሆኑንም ተናግረዋል።

ብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት የወጣቱን የሥራ ባህል በማጎልበት ብሎም ሀገራዊ አንድነትንና የማህበረሰቡን ትስስር በማጠናከር በሀገር ግንባታና ዘላቂ ሰላም ተግባራት ላይ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ እያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም