ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት አርአያ የሚሆን ተግባር እያከናወነች ነው

አዲስ አበባ ፤ግንቦት 17/2017 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት አርአያ የሚሆን ተግባር እያከናወነች እንደምትገኝ የአፍሪካ ህብረት የዘላቂ ከባቢ አየር እና ብሉ ኢኮኖሚ ዳይሬክተር ሃርሰን ንያምቤ ገለጹ።

ዳይሬክተሩ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ አማካኝነት ደረቅ ቦታዎችን አረንጓዴ በማልበስ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ በመከላከል እና ዘላቂ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኗን ለኢዜአ ገልጸዋል።

አረንጓዴ አሻራ የአፍሪካ ህብረት እየተገበረ ለሚገኘው “የታላቁ አረንጓዴ ግንብ ኢኒሼቲቭ” ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አመልክተዋል።

ከአፍሪካ ሕብረት ዋነኛ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነው ይህ ኢንሼቲቭ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2007 የተጀመረ ሲሆን፤ ዓላማውም የሰሃራ በረሃ መስፋፋትን ለመከላከልና በቀጣናው የሚገኙ አገራትን ኢኮኖሚ ማሻሻል ነው።

የአረንጓዴ አሻራ የተስፋ ጮራ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ከኢኒሼቲቩ ትምህርት ሊወስዱ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ኢኒሼቲቭ ስራዎቿ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ልምዷን እንድታካፍል እና የእውቀት ሽግግር እንድታደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

እንደ አረንጓዴ አሻራ ያሉ መሰል ኢኒሼቲቮች በአየር ንብረት ለውጥ ፈተና ውስጥ የማይበገር አቅም ለመገንባት እና ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ ወሳኝ ናቸው ብለዋል ዳይሬክተሩ።

በሌላ በኩል የመንግስት እና የግሉ ዘርፍ በረሃን ጨምሮ ደረቅ ስፍራዎችን በማልማት ወደ ኢኮኖሚ እድሎች በመቀየር ዘላቂ ከባቢ አየርን የመፍጠር ጥረት በተጠናከረ ሁኔታ ሊደግፉ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የልማት አጋሮች በአፍሪካ ለሚከናወኑ የአረንጓዴ ልማት ስራዎችን የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያደርጉ እና የማህበረሰብን አቅም የሚገነቡ ስራዎችን እንዲያከናውኑ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም