የአፍሪካውያንን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የአመራር ሚና ወሳኝ ነው-አቶ ዛዲግ አብርሃ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካውያንን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የአመራር ሚና ወሳኝ ነው-አቶ ዛዲግ አብርሃ
አዲስ አበባ፤ግንቦት 16/2017 (ኢዜአ)፦የአፍሪካውያንን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የአመራር ሚና ወሳኝ መሆኑን የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚዳንት ዛዲግ አብርሃ ገለጹ።
በፈረንጆች 1963 የተመሰረተው የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት 62ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ዛሬ በአፍሪካ አመራር ልዕቀት አካዳሚ በተለያዩ የፓናል ውይይቶች ተከብሯል።
የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚዳንት ዛዲግ አብርሃ በዚሁ ወቅት፤ አፍሪካ ያላትን እምቅ ጸጋ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት በአግባቡ ሳትጠቀም መቆየቷን አውስተዋል።
የአፍሪካ የድህነት ምንጭ የትምህርትና የስልጠና አሰጣጥ ስርዓቱ ስብራት ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ ይህን ስብራት መጠገን ለነገ የማይባል ተግባር ነው ብለዋል።
የአፍሪካውያንን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም የአመራር ሚና ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በአህጉሪቱ የአመራር ብቃትን የማሳደግ ዓላማ ይዞ የተነሳው የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ፤አፍሪካ የሀብቷ እና የሰላሟ ባለቤት እንድትሆን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተለይ ከአጋር አህጉራዊ ተቋማት ጋር በመተባበር የአህጉሪቱን ወጣቶች በፓን አፍሪካኒዝም አስተሳሰብ በመቃኘት ለነገ በሚመጥን መልኩ እያዘጋጀ እንደሚገኝ አንስተዋል።
በዚህም አበረታች ውጤቶች እየተገኙ መሆኑን ጠቅሰው፥በቀጣይም ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) የኢትዮጵያ ተጠሪ አቶ አበባው ቢሆነኝ፥ አፍሪካ የተለያዩ ባህልና ቋንቋዎች ማህደር እንዲሁም የበርካታ ተፈጥሮ ሐብቶች ባለቤት ናት ብለዋል፡፡
እነዚህን ሐብቶች በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል ቅንጅታዊ ስራ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ በአመራር ልማት ዘርፍ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ጠቅሰው፥ ኢጋድም የበኩሉን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና አጋርነት ዳይሬክተር ኢንጅነር መስፍን ደሴ በበኩላቸው፥ወጣቶች የመድረኩ ተሳታፊ መሆናቸው በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ ይዘው እንዲሰሩ ያግዛቸዋል ብለዋል፡፡