ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና ብራዚልን ግንኙነት ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው -ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ግንቦት 16/2017 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያና ብራዚልን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማሳደግ በበርካታ የትብብር መስኮች እየተሰራ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመራ ልዑክ በምግብ ዋስትና፣ረሃብን በመዋጋት እና በገጠር ልማት አጀንዳዎች ላይ ባተኮረው ሁለተኛው የብራዚል እና አፍሪካ ጉባኤ ላይ ተሳትፏል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ፥ ኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ዓመታት በግብርናው ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራትና የተመዘገቡ ስኬቶችን በተመለከተ ተሞክሮዋን ማቅረቧን ገልጸዋል።

የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በተለይ በስንዴ ምርትና በሌማት ትሩፋት ከፍተኛ ስኬት እያስመዘገበች መሆኗን የጉባኤው ተሳታፊዎች መገንዘባቸውንም ነው ያነሱት ያነሱት።

ከጉባኤው በተጓዳኝ ከብራዚል ምክትል ፕሬዝዳንት ጋር መወያየታቸውን ያነሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ሁለቱ ሀገራት በንግድ፣ ኢንቨስትመንት እና በግብርና እና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ተናግረዋል።

የብራዚል ምክትል ፕሬዝዳንት ኢትዮጵያ በዲጅታላይዜሸን፣ በግብርና ላይ በተለይም በስንዴ፣በሌማት ትሩፋት እና በአረንጓዴ አሻራ እያከናወነች ያለውን ስራ አድንቀዋል ነው ያሉት።

የሁለቱን ሀገራት የግብርና ትብብር ለማሳደግም የመግባቢያ ስምምነት መፈረሙን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና ብራዚል የጋራ ዕድገታቸውን በሚወስኑ የትብብር መስኮች ላይ በጋራ መስራት የሚያስችሉ ውይይቶችን በማድረግ መግባባት ላይ መደረሱንም ተናግረዋል።

የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማሳደግ እየሰራን ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ስራዎችን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

ኢትዮጵያም በብሪክስ ማዕቀፍ በሁለትዮሽና በብዝኃ ዘርፍ መድረኮች ከብራዚል ጋር ንቁ ተሳትፎ እንደምታደርግ ጠቁመዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፥ በብራዚል ስድስት የግብርና እና የቴክኖሎጂ ተቋማትን ከልዑካቸው ጋር በመሆን መጎብኘታቸውን አንስተው፥ የብራዚል ብሔራዊ አቅርቦት ኩባንያ በምርት አቅርቦት ሰንሰለት ያለው ሚና ልምድ የተቀሰመበት መሆኑን ገልጸዋል።

የግብርና ምርምር ኮርፖሬሽናቸውም በሁሉም የግብርና ልማት ዘርፎች የሚታዩ ውስንነቶችን የሚቀርፉ ምርምሮችን በማድረግ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ መሆኑን መመልከታቸውንም አንስተዋል።

የብራዚል የግብርና ዕድገት በጥናትና ምርምር የተደገፈ መሆኑ የላቀ ውጤት እንዲያስመዘግብ ማድረጉን ትልቅ ትምህርት ወስደንበታል ነው ያሉት።

በሌላ በኩል የቴክኖሎጂ ፈጠራ ፓርክን መጎብኝታቸውን በማንሳት፥ ከስታርትአፕ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ተቋማትን በአንድ አካባቢ በመክፈት የቴክኖሎጂ ከተማ እየገነባ መሆኑን ተመልክተናል ብለዋል።

በኢትዮጵያ በኩልም በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በሳይበር ደህንነት እና በአይሲቲ ፓርክ እና በአጠቃላይ ዲጅታል ዘርፍ ላይ ያለውን እንቅስቃሴ ተሞክሮ እንደገለጹላቸው አንስተዋል።

የተለያዩ አውሮፕላኖችን ከሚያመርት የአቪየሽን ኩባንያ ጋርም አብሮ ለመስራት የሚያስችል ውይይት መደረጉን ጠቅሰው፥ ኩባንያው ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ንግግር መጀመሩን እንዳስረዳቸው ጠቅሰዋል።

በአጠቃላይ የብራዚል ጉብኝታቸው የሁለቱን ሀገራት የወደፊት እጣፈንታና አብሮ የመስራት እድል የሚያጠናክርና ስኬታማ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም