ቀጥታ፡

የመንግስት ሰራተኞችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት በትኩረት ይሰራል -የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 16/2017(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ከተማ የመንግስት ሰራተኞችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ገለጸ።

ቢሮው የመንግሥት ሠራተኞችን የቤት ባለቤት ለማድረግ የሚያስችል የውል ስምምነት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ተፈራርሟል።

የቢሮው ሃላፊ ቅድስት ወልደጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ በፈረሙት ስምምነት መሰረትም ከ41 ሺህ በላይ የመንግስት ሰራተኞች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተመላክቷል።

የከተማ አስተዳደሩ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ሃላፊዋ እንደገለጹት የመግባቢያ ስምምነቱ የመንግስት ሰራተኞችን የመኖሪያ ቤት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ያለመ ነው።

የቤት ዕድሉ የቅድሚያ ተጠቃሚ ለመሆን በማህበር ተደራጅተው ቅድመ ሁኔታዎችን ያሟሉት የከተማዋ መምህራን መሆናቸውም ተገልጿል።


 

በስምምነቱ መሰረትም የመንግስት ሰራተኛው 25 በመቶ ቆጥቦ ባንኩ 75 በመቶ ብድሩን የሚያመቻች መሆኑንና ብድሩ የሚሰጠው በዝቅተኛ የወለድ መጠን መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ በበኩላቸው ስምምነቱ መሰረታዊ ለውጥ እንደሚያመጣ የታመነበት መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም ባንኩ 120 ቢልዮን ብር በዘቅተኛ የወለድ መጠን ለማቅረብ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) የከተማ አስተዳደሩ መምህራን የቤት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ወቅቱ በሚፈልገው ልክ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።

በዚህም ከ23ሺህ በላይ መምህራን በ350 ማህበራት ተደራጅተው የብድር አቅርቦት ለማግኘት ጥረት ሲደረግ እንደቆየም አንስተዋል።


 

በመምህራን ላይ የሚሰራ ስራ የትውልድ ጥያቄን መፍታት መሆኑን ጠቁመው አሁንም በከተማ አስተዳደሩ ስር ያሉ ያልተደራጁ መምህራን እንዲደራጁ ጥሪ አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መምሀራን ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ድነቃለም ቶሎሳ ቤት የመምህራን ሁለተኛው መስሪያ ቤታቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ስምምነቱ ለዓመታት መምህራን ሲያቀርቡ ለነበረው ጥያቄ ምላሽ የሰጠ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም