ሴቶችን በማብቃት ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሴቶችን በማብቃት ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ ነው
አዲስ አበባ፤ግንቦት 16/2017 (ኢዜአ)፦ሴቶችን በማብቃት ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ እና የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ ፕሬዝዳንት ዘሃራ ኡመድ ገለጹ።
የማህበራት ጥምረት ለፍትህ እና ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ በሚል መሪ ሀሳብ ሦስተኛው የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን አገር አቀፍ ጠቅላላ ጉባኤ ተካሄዷል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ እና የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ ፕሬዝዳንት ዘሃራ ኡመድ በወቅቱ እንደገለጹት፥ ሴቶችን ማብቃት እና በሁሉም ዘርፍ ተጠቃሚ ማድረግ የአንድ ተቋም ወይም አደረጃጀት ተግባር ብቻ ሳይሆን የጋራ አገራዊ ሀላፊነት ነው።
የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን በሁሉም መስክና ሁኔታ የሚገኙ ሴቶችን ለማገልገል ያለው ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ እና የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ትብብራቸው ጠንካራ እና ውጤታማ ሆኖ መቋየቱን አንስተው፥ የጋራ ግብን ለማሳካት በአብሮነት በቀጣይ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።
የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂክማ ከይረዲን በበኩላቸው፥በለውጡ ዓመታት የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማሳደግ በተሰሩ ስራዎች አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
በዚህም ሴቶች በፖለቲካዊ ተሳትፎና በአመራር ሰጪነት በብዛት መሳተፋቸውን ለአብነት አንስተዋል።
ለተገኘው ውጤት የሴቶች አደረጃጀት ትልቅ ሚና እንዳለው አንስተው፤ በቀጣይ የሚሠራውን ስራ መንግስት ሁለንተናዊ ድጋፍ ለፌዴሬሽኑ ያደርጋል ብለዋል።
የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ ተሳታፊነት እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የድርሻችንን ለመወጣት ተንቀሳቅሰናል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ተወካይ ፕሬዚዳንት አስካለ ለማ ናቸው።
ፌዴሬሽኑ በሰራው ስራ የአባላትን ቁጥር ወደ ስምንት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ከፍ ማለቱን ጠቁመው፤ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ እየጨመረ መሆኑን ተናግረዋል።
የሴቶች ፌዴሬሽን በኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ሰፊ ስራ ያከናወነ ሲሆን፤ በዚህም ሴቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እያደገ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲያድግ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በመድረኩ ላይ መልዕክታቸውን ካስተላለፉ የሲቪል ማህበራት እና አጋር ድርጅቶች መካከል የሰራተኛ ኮንፌድሬሽን ፕሬዝዳንት ካሳሁን ፎሌ፣ የሠራተኞች የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳምሶን ቢራቱ ፣የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የሴቶች ክንፍ ሰብሳቢ እጸገነት ተስፋዬ እንዳገለጹት፥ ሴቶች በፖለቲካ የኢኮኖሚ የማህበራዊ ዘርፍ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ይበልጥ እንዲያድግ በትኩረት እየሰሩ መሆኑን አንስተዋል።
በቀጣይም የሴቶች ፌዴሬሽን በሚሰራው ስራ የሚያስፈልገውን ድጋፍ ለመስጠት እንዲሁም የጋራ ስራ ለማጠናከር ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።