ቀጥታ፡

አርሰናል እና ባርሴሎና የአውሮፓ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ዋንጫን ለማንሳት ይፋለማሉ 

አዲስ አበባ ፤ግንቦት 16/2017 (ኢዜአ)፡- የ2024/25 የአውሮፓ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ ዛሬ በአርሰናል እና ባርሴሎና መካከል ይደረጋል።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ምሽት 1 ሰዓት ላይ በፓርቹጋል ሊዝበን ጆሴ አልቫላዴ ስታዲየም ይካሄዳል።

በግማሽ ፍጻሜ ጨዋታው ባርሴሎና ቼልሲን፣ አርሰናል ሊዮንን በማሸነፍ ለዛሬ ጨዋታ ደርሰዋል።

አርሰናል የአውሮፓ ሴቶች  ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ያነሳ ብቸኛው የእንግሊዝ ክለብ ነው።

የሰሜን ለንደኑ ክለብ ለሁለተኛ ጊዜ ዋንጫውን ለማንሳት ከስፔኑ ኃይል ቡድን ጋር ይፋለማል።

ባርሴሎና ሶስት ጊዜ የሻምፒዮንስ ሊጉን ዋንጫ ያነሳ ስኬታማ ክለብ ሲሆን ላለፉት ሁለት ተከታታይ ዓመታት የውድድሩ ዋንጫ ባለቤትም ነው።

የካታላኑ ክለብ ተጋጣሚውን ካሸነፈ በውድድሩ ታሪክ ዋንጫውን ለሶስት ተከታታይ ዓመት ያነሳ የመጀመሪያው ቡድን ይሆናል።

አርሰናል እና ባርሴሎና ከዚህ ቀደም አራት ጊዜ በሻምፒዮንስ ሊጉ ተገናኝተው ቡድኖቹ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ አሸንፈዋል።

የ39 ዓመቷ ክሮሺያዊ ኢቫና ማርቲንቺች ተጠባቂውን የፍጻሜ ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም