ቀጥታ፡

የመኖሪያ ቤታችን መታደሱ ቀሪ ኑሯችንን ምቹ በሆነ ቦታ እንድንኖር አድርጎናል-የበጎ ፈቃድ ተጠቃሚዎች

አዲስ አበባ፤ግንቦት 16/2017(ኢዜአ)፦የመኖሪያ ቤታችን በበጎ ፈቃደኞች መታደሱ ቀሪ ኑሯችንን ምቹ በሆነ ቦታ እንድንኖር አስችሎናል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሰው ልጅ የህሊና እርካታ ለማግኘት ያለምንም ቀስቃሽ በእራሱ ተነሳሽነት የሚፈፅመው ተግባር ነው፡፡

ይህ ተግባርም ማህበራዊ ትስስርን፣ አንድነትና ፍቅርን የበለጠ ከማጠናከሩም በላይ በቤት እድሳት፤ ደካሞችን በመርዳትና በሌሎች ተግባራት በመሰማራት የዜጎችን ችግር በዘላቂነት እየፈታ ይገኛል።

ኢዜአ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፈለ ከተማ እና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በተለያዩ በጎ አድራጊዎች ቤታቸው የታደሰላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች አሁን ያሉበትን ሁኔታ በተመለከተ ቃለመጠይቅ አድርጓል።

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፈለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ቀሲስ ይትባረክ ወርቄ ከዚህ ቀደም ይኖሩበት የነበረው ለሰው ልጅ ለመኖር ምቹ ባልሆነ ከቤተሰባቸው ጋር ሲኖሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

ነገር ግን ቤተሰብን ከመምራት ባለፈ የመኖሪያ ቤቱን ለማደስ የአቅም ውስንነት በመኖሩ መኖሪያውን ምቹ ለማድረግ አለመቻላቸውን ተናግረዋል።

ሌላኛዋ የዚሁ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ መዲና ጊቤ ልጆቻቸውን የቤት ግርግዳ በሚፈርስበት እና ልጆች እንደልባቸው ተጫውተው ለማደግ አስቸጋሪ በሆነበት ቤት ስኖር ቆይቻለሁ ይላሉ።

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ፀሀይ ታደሰ በበኩላቸው፥ አራት ልጆቻቸውን ለመኖሪያ አዳጋች በሆነ ቤት ውስጥ አሳድጌያለሁ ብለዋል።

አሁን ላይ ያ ሁሉ ችግር ተቀርፎ ቀና ልብ ባላቸው በጎ ፈቃደኞች ቤታቸው ታድሶላቸው ኑሮአቸውን በማረ ቤት በደስታ እየኖርኩ እገኛለሁ ይላሉ።

በተመሳሳይ የክረምት ወቅት በመጣ ቁጥር ዝናብ በሚያስገባና ለፍሳሽ ተጋላጭ በሆነ ቤት ውስጥ ከሚስቱ እና ከአንድ ልጁ ጋር ህይወትን ስገፋ ነበረ ያሉት ደግሞ አቶ ዳዊት ካሳ ናቸው።

ኢትዮጵያዊያን እርስ በእርስ የመረዳዳት ባህል ከጥንትም ጀምሮ ያለ መሆኑን ገልጸው፤ ሰብአዊ ተግባርን የሚሰሩ ሰዎች የጀመሩትን ስራ በማጠናከር የአቅመ ደካማና አረጋውያን ዜጎችን ቤት ለማሻሻል የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ቀሲስ ይትባረክ ጥሪ አቅርበዋል።

አቶ ዳዊትም በፊት ከነበሩበት አስቸጋሪ የመኖሪያ ስፍራ ተላቆ ወደ አማረ ቤት መኖር በመቻላቸው አእምሮዬ ሰላም እንዲሰማኝ አድርጓል ብለዋል።

በመዲናዋ የሚከናወኑ የበጎ ፈቃድ ስራዎች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የምንገኝ ሰዎችን መታገዝ የምንችልበትን ሁኔታ ያጎለበተ ነው ሲሉ የተናገሩት ወይዘሮ መዲና ጊቤ ናቸው።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስተባበሪያ ዳይሬክተር ዳዊት ሙሉጌታ፥ በዘንድሮው የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን ባለሀብቶች እና የተለያዩ ተቋማትን በማሳተፍ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ከተሰሩ ስራዎች መካከል የአቅመ ደካማና የአረጋውያን ቤት ማደስ ፣ ደም መለገስ፣ ማዕድ ማጋራት ብሎም የመንገድ ትራፊክ አገልግሎት ተጠቃሽ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በተለይም በበጋው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በአስቸጋሪ የመኖሪያ ቤትና አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎችን ካለባቸው ችግር ለማላቀቅ የተለያዩ በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ በተሰራው ስራ በመዲናዋ ከ5 ሺህ በላይ ቤቶችን ማደስ ተችሏል ብለዋል።

በሁለቱ ክፍለ ከተሞች በበርካታ የበጎ ፈቃድ አይነቶች በመሳተፍ ላይ ያሉት በጎ ፈቃደኛ ራሄል ገዛኸኝ እና ሙከሚል አብዶ በበኩላቸው፥ በሚሰሩት የበጎ ፈቃድ ሰዎች ተጠቃሚ ሲሆኑ ሲመለከቱ ውስጣቸው ደስታ እንደሚሰማቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም