ኢትዮጵያ የሥራ ዕድል ፈጠራን ታሳቢ ያደረጉ የልማት እንቅስቃሴ ውጤቶችን በተግባር እያሳየች ነው - ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የሥራ ዕድል ፈጠራን ታሳቢ ያደረጉ የልማት እንቅስቃሴ ውጤቶችን በተግባር እያሳየች ነው - ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 15/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የሥራ ዕድል ፈጠራን ታሳቢ ያደረጉ እና የአጀንዳ 2063 የልማት ግቦችን የሚያሳኩ የልማት እንቅስቃሴ ውጤቶችን በተግባር እያሳየች መሆኑን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ፡፡
"የማይበገር ማህበረሰብ እና ጤናማ አካባቢ የሰው ኃይልን በብዛት የሚጠቀሙ የኢንቨስትመንት ፕሮግራም አካሄዶች" በሚል መሪ ሀሳብ ከግንቦት 10 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በአፍሪካ ሕብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ ሲካሄድ የቆየው 20ኛው የዓለም ሥራ ድርጅት አህጉራዊ ስብሰባ ዛሬ ተጠናቋል፡፡
ከ50 በላይ የዓለም ሀገራት ተወካዮች፣ 30 የአፍሪካ ሚኒስትሮች፣ ከሁለት ሺህ በላይ ተሳታፊዎች የታደሙበት ስብሰባ የአዲስ አበባ ቃል ኪዳን በሚል የጋራ የአቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡
የአዲስ አበባ ቃል ኪዳን በዋናነት የሰው ሀይልን በብዛት በሚጠቀሙ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ በማተኮር ለተግባራዊነቱ ክህሎትን በቴክኖሎጂ ማዳበርና ጠንካራ ትብብር ለመፍጠር የጋራ ስምምነት የተደረሰበት ነው፡፡
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ጉባኤውን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፤ በአፍሪካ ማንኛውም የልማት ሥራ የሥራ ዕድል ፈጠራን ታሳቢ ያደረገ መሆን እንዳለበት ስምምነት መደረሱን ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ቃል ኪዳን የሰው ጉልበትን የሚጠቀሙ ስራዎች ላይ ማተኮርና ክህሎትን በቴክኖሎጂ ማጎልበት የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 የተቀመጡ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ከንግግር ባለፈ የተግባር እርምጃ መውሰድ ያስችላልም ብለዋል፡፡
ከአጀንዳ 2063 የዘላቂ የልማት ግቦች ጋር በቀጥታ ግንኙነት ያለውና በየጊዜው ክትትል የሚደረግበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በአፍሪካ የልማት ሥራዎች ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የተሳሰሩ እንዲሁም በልማት የሚውሉ የፋይናንስ ምንጮች የሥራ ዕድል ፈጠራን ከግምት ውስጥ ያስገቡ እንዲሆኑ አቅጣጫ መቀመጡንም ገልጸዋል፡፡
ከአዲስ አበባ ቃል ኪዳን በፊት ኢትዮጵያ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ከፍተኛ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችሉበትን ብሔራዊ መርሃ ግብር ገቢራዊ ማድረጓንም ጠቅሰዋል፡፡
በመላ ሀገሪቱ በገጠርና በከተማ የሚከናወኑ የግንባታ ፕሮጀክቶች ሰፊ የሰው ሀይል የሚጠቀሙ በመሆናቸው ደህንነትን ታሳቢ በማድረግ ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል፡፡
የስብሰባው ተሳታፊዎች በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወኑ የመሰረተ ልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው በመጎብኘት የኢትዮጵያን ቁርጠኝነት መታዘብ መቻላቸውንም ገልጸዋል፡፡
በተለይም በመንገድ መሰረተ ልማት የሚከናወኑ ሥራዎች የሰው ሀይል የሚጠቀሙ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ከፍተኛ የሥራ እድል እየፈጠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል የማይበገር ማህበረሰብ የመገንባት ሂደቱም ውጤት የታየበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መሀመድ አብዱራህማን በበኩላቸው፤ አካታች፣ ጥራት ያለውና ዘላቂ የሥራ እድል መፍጠር የሁሉም አፍሪካውያን ወቅታዊ አጀንዳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በ20ኛው የዓለም ሥራ ድርጅት አህጉራዊ ስብሰባ በመንገድ ፕሮጀክቶች ያከናወኗቸውን ሰው ተኮር ሥራዎች አቅርባለች ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የመሰረተ ልማት ስራዎች በሚገባቸው ልክ የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ለአብነት በጊንጪ የሰው ሃይል መጠቀም ላይ ትኩረት ያደረገው ማሰልጠኛ ተቋም የሥራ ዕድል የሚፈጥሩና ምርታማነትን የሚጨምሩ ስልጠናዎች እየተሰጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሰው ሀይል የሚከናወኑ ሥራዎችን በቴክኖሎጂ በመደገፍ የሚፈለገውን ግብ ለማሳካት ጥረት ይደረጋልም ብለዋል፡፡