መምህራን የተሻለ ትውልድን በመቅረጽ ለሀገር ግንባታ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ማጠናከር አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
መምህራን የተሻለ ትውልድን በመቅረጽ ለሀገር ግንባታ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ማጠናከር አለባቸው
ነቀምቴ/ጅማ፤ ግንቦት 15/2017(ኢዜአ)፦ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን የተሻለ ትውልድን በመቅረጽ ለሀገር ግንባታ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ማጠናከር እንዳለባቸው ተመለከተ።
በወለጋ እና ጅማ ዩኒቨርሲቲዎች ''ትውልድ በመምህር ይቀረፃል፤ ሀገር በትምህርት ይበለጽጋል'' በሚል መሪ ሀሳብ መምህራን የተሳተፉበት ውይይት ተካሂዷል።
በወለጋ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው ውይይት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ተስፋዬ ለማ(ዶ/ር)፣ መምህራን ትውልድን በመቅረጽ ሀገርን የሚያበለጽግ ዜጋ የመፍጠር ኃላፊነታቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው አመልክተዋል።
ዩኒቨርሲቲው የተሻለ ትምህርት የሚሰጥበት ስፍራ ለማድረግና የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የሚያግዙ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው እያከናወነ ያለው ተግባር ስኬታማ የሚሆነው መምህራን የተሻለ ትውልድ ለመገንባት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሲጠናከር መሆኑንም ገልጸዋል።
በመሆኑም መምህራን የተሻለ ትውልድን በመቅረጽ ለሀገር ግንባታ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ማጠናከር አለባቸው ብለዋል።
በውይይት መድረኩ የተገኙት በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል የከተሞች ክላስተር አስተባባሪ መስፍን መላኩ፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ትውልድን ከመቅረጽ አንጻር ትልቁን ድርሻ ይወጣሉ ሲሉ ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲው መምህራን ሙሉ ጊዜና ጉልበታቸውን በትውልድ ግንባታ ላይ በማዋል የሀገር ግንባታ ሂደቱን ማጠናከር እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
በተመሳሳይ በጅማ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደ ውይይት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ጀማል አባፊጣ(ዶ/ር) መምህራን ኢትዮጵያ የያዘችው የልማትና የሰላም ግንባታ ሂደት እንዲፋጠን የበኩላቸውን ድርሻ ማበርከት አለባቸው ብለዋል።
እንደ ሀገር በማህበራዊ፣ በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በዲፕሎማሲው መስክ የተመዘገቡ ውጤቶችን ለማስቀጠል መምህራን ያላቸውን ሙያዊ አስተዋፅኦ ማጎልበት እንዳለባቸውም አስረድተዋል።
የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት በኩልም በትምህርት ዘርፉ የተጀመረውን የሪፎርም ስራ ለማስቀጠል ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
በውይይት መድረኮቹ ላይ የተሳተፉ መምህራንም የትምህርት ጥራት እንዲጠበቅ በማድረግ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ ለመፍጠር የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።