ጉባኤው የአፍሪካ ሀገራት የኢትዮጵያን የዲጂታል መታወቂያ ትግበራ ልምድ ለመቅሰም ጥያቄ ያቀረቡበት ነው - ብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም - ኢዜአ አማርኛ
ጉባኤው የአፍሪካ ሀገራት የኢትዮጵያን የዲጂታል መታወቂያ ትግበራ ልምድ ለመቅሰም ጥያቄ ያቀረቡበት ነው - ብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 15/2017(ኢዜአ)፦ አይ ዲ ፎር አፍሪካ ጉባኤ የአፍሪካ ሀገራት ኢትዮጵያ በሀገር በቀል ዕውቀት አልምታ ከተገበረችው የዲጂታል መታወቂያ ልምድ ለመቅሰም ጥያቄ ማቅረባቸውን የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዮዳሔ አርአያሥላሴ ገለፁ።
ለአራት ተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ የነበረው አይ ዲ ፎር አፍሪካ ዓመታዊ ጉባኤ ተጠናቋል።
በጉባኤው የተለያዩ ሀገራት በዲጂታል ማንነትና መሰረተ ልማት ግንባታ ያላቸውን ተሞኮሮ ያካፈሉባቸው የፖናል ውይይቶችና ባዛሮች መካሄዳቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያም በሀገር በቀል ዕውቀት በታገዘ ቴክኖሎጂ ይፋ ያደረገችው ዲጂታል መታወቂያ የበርካታ አፍሪካ ሀገራትን ቀልብ ስቧል።
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዮዳሔ አርአያሥላሴ የጉባኤውን መጠናቀቅ አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ሀገር በቀል ዕውቀትን ተጠቅማ ያለማችው የዲጂታል መታወቂያ ቴክኖሎጂ ከበርካታ ሀገራት አድናቆት እንደተቸረው ተናግረዋል።
በዚህም በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ኢትዮጵያ በዲጂታል መታወቂያ ያካበተችውን የቴክኒክና የዕውቀት ድጋፍ መጠየቃቸውንና ኢትዮጵያም ከጉባኤው ተሳታፊ ሀገራት ልምዶች መቅሰሟን ገልጸዋል።
የአይ ዲ ፎር አፍሪካ መስራችና ሊቀመንበር ጆሴፍ አቲክ(ዶ/ር) በበኩላቸው ጉባኤው የአፍሪካን የዲጂታል ሽግግር ስኬትና ቀሪ ስራዎች ላይ ባለድርሻ አካላት በስፋት መምከራቸውን ተናግረዋል።
በአፍሪካ የዲጂታል ማንነት ግንባታ እያደገ መምጣቱን ገልፀው፤ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የተሻለ አፈፃፀም ማሳየቷን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት ያከናወናቸው ተግባራት ለዲጂታል ሽግግር የሰጠውን ትኩረት ያመላክታል ሲሉም ገልጸዋል።
አይ ዲ ፎር አፍሪካ ዓመታዊ ጉባኤ ከሁለት ሺህ በላይ የተለያዩ ሀገራት ተሳታፊዎች የታደሙበት ነበር።