ቀጥታ፡

በመጪው ክረምት በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ የዝናብ ሁኔታ ይኖራል

አዳማ፤ ግንቦት 15/2017 (ኢዜአ)፡- በመጪው ክረምት በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ የዝናብ ሁኔታ እንደሚኖር የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ የበልግ ወቅት ትንበያውና በተጨባጭ የተከሰተውን ሁኔታ በማነጻጸር ከአገልግሎቱ ተጠቃሚዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር ለመገምገምና የመጪውን ክረምት የአየር ሁኔታ ትንበያ ይፋ ለማድረግ ያዘጋጀው መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ይገኛል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ፈጠነ ተሾመ እንደገለጹት፤ መድረኩ የተዘጋጀው በዋናነት የበልግ ወቅት የትንበያ ግብረ-መልስና የመጪው ክረምት ትንበያን ለመስጠት ነው።


 

በዚህም የበልግ ወቅት ትንበያችን ከነባራዊ ሁኔታው ጋር ሲነፃፀር የተጣጣመ ሆኖ አግኝተነዋል ብለዋል።

አቶ ፈጠነ አክለውም በመጪው ክረምት የዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

ይህም በክረምት ወቅት ለሚከናወኑ የግብርና ስራዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቅሰው፤ በመስኖ ታግዞ ለሚከናወኑ ስራዎችም በቂ የውሃ አቅርቦት እንዲኖር ያስችላል ነው ያሉት።

እንዲሁም ለተፋሰሶች፣ ለግድቦች፣ ለኢነርጂ ፍላጎት በቂ ውሃ ለሚይዙትም ይረዳል ያሉት አቶ ፈጠነ፤ በአንጻሩ ደግሞ ተደጋጋሚና ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ሊጥል ስለሚችል ከወዲሁ ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስበዋል።

በመሆኑም በዚህ ምክንያት ሊከሰት ስለሚችለው የጎርፍ አደጋ ተፋሰሶች፣ የውሃ አስተዳደሮች በተሰጠው ትንበያ መሠረት ሊያጋጥሙ የሚችሉትን አደጋዎች ለመከላከል መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የጎርፍ ተጋላጭ አካባቢዎች አስፈላጊውን የውሃ ማፋሰሻ ቦዮች በማዘጋጀት ከወዲሁ አጠናክረው እንዲያስቀጥሉ አስገንዝበዋል።


 

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ አቶ ሞቱማ መቃሳ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ የተሰጠውን ተግባርና ሀላፊነት በተሻለ ብቃት እየተወጣ መሆኑን አስታወቀዋል።

ለዚህም ከልማት አጋሮችና ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት በመስራት የማስፈፀም አቅሙን ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እያሳደገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በዛሬው እለት ኢንስቲትዩቱ ይፋ የሚያደርገውን የቀጣይ ክረምት ወራት የአየር ጸባይ ትንበያ የአጭርና ረጅም ጊዜ ትንበያዎችን መሠረት በማድረግ የሚሰጠውን ምክረ-ሀሳብ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም