የሚዲያና ኮሙንኬሽን ባለሙያዎች ገዢ ትርክቶችን በማጽናት አብሮነትን ማጎልበት ይገባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
የሚዲያና ኮሙንኬሽን ባለሙያዎች ገዢ ትርክቶችን በማጽናት አብሮነትን ማጎልበት ይገባቸዋል
ሐረር፤ግንቦት 15/2017 (ኢዜአ)፦የሚዲያና ኮሙንኬሽን ባለሙያዎች በዘገባቸው ገዢ ትርክቶችን በማጽናት ህብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትንና አብሮነትን ማጎልበት ይገባቸዋል ሲሉ በብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ ገለጹ።
"የድህረ እውነት ዘመንን በእውቀትና በእውነት" በሚል መሪ ሃሳብ ለሐረሪ ክልል አመራሮች፣ ለሚዲያና ኮሙንኬሽን ባለሙያዎች ስልጠና መሰጠት ተጀምሯል።
በስልጠናው መክፈቻ ላይ የተገኙት በብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ እንዳሉት፥ መንግሥት የሚያከናውናቸው የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች ለህዝብ እንዲደርስ ከማድረግ አንጻር የሚዲያና ኮሙንኬሽን ባለሙያዎች የጎላ ሚና አላቸው።
በአሁኑ ወቅት የአመለካከት ጥራትን በማጎልበትና እውነት ላይ የተመሰረተ መረጃን ለህዝቡ በማድረስ የተጀመሩ ስራዎችን ማጠናከር ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
በተለይም ገዢ ትርክቶችን የሚያንጹ እና ለህብረ ብሔራዊ፣ ለዴሞክራሲ እና ለተቋም ግንባታ ገንቢና ጠቃሚ መረጃዎችን መቅረጽ እና ተግባራዊ የሆነ ስራ ማከናወን ይገባል ብለዋል።
በክልሉ ያሉ የልማት ስራዎችን በማስተዋወቅና በመግለጽ የገጽታ ግንባታ ስራ ማበልጸግ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።
ስልጠናው የኮሙኒኬሽንና የሚዲያ ባለሙያዎች ገዢ ትርክቶችን በማጽናት ህብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትንና አብሮነትን በማጎልበቱ ረገድ የተጀመሩትን ተግባራት አጠናክረው እንዲያስቀጥሉ የሚረዳ ነው ብለዋል።
በብልጽግና ፓርቲ ህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ወይዘሪት ፈዲላ ቢያ በበኩላቸው፥ በብልጽግና ጉዞ የተያዘውን ራዕይ ከግብ ለማድረስ የድህረ እውነት ዘመንን የተረዳ የሚዲያና ኮሙንኬሽን ስራ እጅግ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የሚዲያና ኮሙንኬሽን ባለሙያዎች እንዲሁም አመራሩ አሁን እየተከናወነ የሚገኘውን የልማት ስራዎች እና ህብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነትን ማበልጸግ ይገባቸዋል ሲሉም ተናግረዋል።
በተለይም እንደ አገር የሚከናወኑ የልማት ስራዎችን በሚዲያ እና በኮሙኒኬሽን ስራዎች በማጎልበት መስራት ይጠበቃል ብለዋል።
ለሶስት ቀናት በሚቆየው ስልጠና በክልሉ የሚገኙ የሚዲያና ኮሙንኬሽን ባለሙያዎች እንዲሁም የክልሉ አመራሮች የተሳተፉ ሲሆን በወቅቱም የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ሰናይት ሀይሌ የውይይት መነሻ ጽሁፍ አቅርበዋል።