በኢትዮጵያ እና በፈረንሳይ መካከል ያለው ትብብር ብዝሃ ዘርፍ ወዳለው ጠንካራ ግንኙነት ተሸጋግሯል- የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ እና በፈረንሳይ መካከል ያለው ትብብር ብዝሃ ዘርፍ ወዳለው ጠንካራ ግንኙነት ተሸጋግሯል- የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 15/2017 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ እና በፈረንሳይ መካከል ያለው ትብብር ብዝሃ ዘርፍ ወዳለው ጠንካራ ግንኙነት መሸጋገሩን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የልዑክ ቡድናቸው በፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኤሊሴ ቤተመንግሥት አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
በሁለትዮሽ ውይይቱ ወቅትም ፕሬዝዳንት ማክሮን በታኅሳስ 2017 ኢትዮጵያን ሲጎበኙ የተደረሱ ስምምነቶችን አፈፃፀም በጋራ መገምገማቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።
ሁለቱ ሀገራት ለረጅም ዘመናት እንደ መከላከያ እና ፀጥታ፣ የባሕል ጥበቃ እና ትምህርት ባሉ ዘርፎች ጠንካራ ትስስር እና ትብብር መፍጠራቸውን ገልጿል።
የሀገራቱ መሪዎች በፓሪስ የነበራቸው ውይይት በኢኮኖሚው መስክ የበለጠ ትብብር ለማድረግ እድሎችን የፈተሸ መሆኑ ተጠቁሟል።
ፈረንሳይ የኢትዮጵያ እዳ ክለሳ ሂደት ቁልፍ ደጋፊ እንደሆነች ጽህፈት ቤቱ በመረጃው አውስቷል።
ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ፈረንሳይ እና ኢትዮጵያ በሁለትዮሽ ግንኙነታቸው መጠናከር ላይ አበክረው መስራታቸውንም እንዲሁ።
ይኽም በከፍተኛ የመሪዎች ጉብኝቶች፣ ስትራቴጂያዊ ስምምነቶች ብሎም በብዙ ዘርፎች በተጀመሩ የጋራ የሥራ ሂደቶች የታየ ሆኖ መቆየቱ ተገልጿል።
ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ ሁለቱም መሪዎች በየሀገራቱ ጉብኝቶችን አካሂደዋል።
በጥቅምት 2011 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ፈረንሳይ ተጉዘው ለተጠናከረው የመከላከያ እና የባሕል ትብብር ስምምነት መሠረት የጣለ ውይይት አድርገው ነበር።
በመጋቢት 2011 ዓ.ም የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ይፋዊ ጉብኝታቸውን በማድረግ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር በርካታ የትብብር ስምምነቶችን ፈርመዋል።
ከስምምነቶቹም የላሊበላ ውቅር አቢያተ ክርስቲያናት እና የብሔራዊ ቤተመንግሥት እድሳት መንገድ የከፈቱ ስምምነቶች እንደሚጠቀሱ ጽህፈት ቤቱ አመልክቷል።
በኢትዮጵያ ቆይታቸውም ፕሬዝዳንት ማክሮን ከጥገና ሥራው መጀመር አስቀድሞ ላሊበላን መጎብኘታቸው የሚታወስ ነው።
በየካቲት 2015 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፈረንሳይን በድጋሚ የጎበኙ ሲሆን የንግድ እና ኢንቬስትመንት ትስስሮች ላይ በማተኮር ውይይቶች ተካሂደዋል።
በወቅቱም ኢትዮጵያ ያላትን የተረጋገጠ ዘላቂ የባሕር በር የማግኘት ፍላጎት ብሎም የቀጣና ሰላም አስፈላጊነት ላይ ውይይት ተደርጓል።
በታኅሳስ ወር 2017 ዓ.ም ፕሬዝዳንት ማክሮን ወደ ኢትዮጵያ በድጋሚ መጥተው ፈረንሳይ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሪፎርም እና የእዳ ክለሳ በተመለከተ ያላትን ድጋፍ በድጋሚ ማረጋጣቸውን ነው ጽህፈት ቤቱ ያስታወቀው።
በጉብኝቱ ፕሬዝዳንት ማክሮን የኢትዮጵያን የእዳ ክለሳ ሥራ በምሉእ መልክ ደግፈው የኢኮኖሚ መረጋጋት እና እድገት ለማምጣት ፈጣን መፍትሔ የመስጠትን አስፈላጊነት አፅንኦት ሰጥተው ነበር በወቅቱ በነበራቸው ቆይታ።
ባለፉት ሰባት አመታት በኢትዮጵያ እና በፈረንሳይ ያለው ግንኙነት ብዝሃ ዘርፍ ወዳለው ጠንካራ ግንኙነት መሸጋገሩንና ይኽም በሁለቱ መሪዎች የነቃ ተሳትፎ የተጠናከረ መሆኑን ጽህፈት ቤቱ አመልክቷል።