የጣልያን ሴሪ አ ዋንጫን ማን ያነሳል? ናፖሊ ወይስ ኢንተር ሚላን? 

አዲስ አበባ ፤ ግንቦት 15/2017(ኢዜአ)፡- የ2024/25 የጣልያን ሴሪ አ ዋንጫን አሸናፊ የሚለዩ ሁለት ወሳኝ ጨዋታዎች ዛሬ ማምሻውን ይደረጋሉ። 

በመጨረሻው የ38ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ናፖሊ ከካግሊያሪ በሜዳው፣ ኢንተር ሚላን ከኮሞ ከሜዳው ውጪ ከኮሞ ጋር በተመሳሳይ ምሽት 3 ሰዓት ከ45 ላይ ይጫወታሉ።

ናፖሊ በ79 ነጥብ ሊጉ እየመራ ነው። ኢንተር ሚላን በ78 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።

የውድድር ዓመቱን ተመጣጣኝ እና ተቀራረቢ ፉክክር ያደረጉት ቡድኖቹ የዋንጫው አሸናፊ ለመሆን የመጨረሻውን ሳምንት መጠበቅ ግድ ብሏቸዋል። 

ናፖሊ በሊጉ ባደረጋቸው 37  ጨዋታዎች 23 ጊዜ ሲያሸንፍ 4 ጊዜ ተሸንፏል። 10 ጊዜ አቻ ወጥቷል። 57 ጎሎችን ሲያስቆጥር 27 ጎሎችን አስተናግዷል። 

ተከታዩ ኢንተር ሚላን  በሊጉ እስከ አሁን ባካሄዳቸው 37 ጨዋታዎች 23 ጊዜ ድል ሲቀናው 5 ጊዜ ተሸንፏል። 9  ጊዜ  ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል። 

ቡድኑ 77 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 35 ግቦች ተቆጥረውበታል።

ናፖሊ ካግሊያሪን ካሸነፈ የኢንተር ሚላንን ውጤት ሳይጠብቅ ዋንጫውን ያነሳል። 

በአንጻሩ የአምናው የሊጉ አሸናፊ ዋንጫውን ለማንሳት ኮሞን አሸንፎ ናፖሊ ነጥብ መጣል ይኖርበታል።

ናፖሊ ተሸንፎ ኢንተር ሚላን አቻ ቢወጣ ሁለቱ ቡድኖች ተመሳሳይ 79 ነጥብ ይኖራቸዋል። 

ቡድኖቹ በዘንድሮው የውድድር ዓመት በነበራቸው ሁለት የእርስ በእርስ ግንኙነቶች በተመሳሳይ አንድ አቻ ተለያይተዋል።

በሊጉ አወዳዳሪ አካል ደንብ መሰረት ሁለት ቡድኖች ተመሳሳይ ነጥብ እና በእርስ በእርስ ግንኙነታቸው እኩል ውጤት ካስመዘገቡ የዋንጫውን አሸናፊ የሚለይ የመጨረሻ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ይደረጋል። 

በዛሬ ምሽት መርሃ ግብር ይህ አጋጣሚ የሚፈጠር ከሆነ አሸናፊ ለመለየት ሁለቱ ቡድኖች የፊታችን ሰኞ ግንቦት 18 ቀን 2017 ይጫወታሉ።   

ከዚህ ቀደም የጣልያን ሴሪ አ ዋንጫን አሸናፊ በጥሎ ማለፍ ሕግ የተለየው በአንድ አጋጣሚ ብቻ ነው።

እ.አ.አ በ1963/64 የውድድር ዓመት ቦሎኛ እና ኢንተር ሚላን በተመሳሳይ 54 ነጥብ እና እኩል የእርስ የእርስ በእርስ ግንኙነት ውጤት በማጠናቀቃቸው ወደ መለያ ጨዋታ አምርተዋል። 

ቦሎኛ ኢንተር ሚላንን 2 ለ 0 በማሸነፍ የስኩዴቶውን ዋንጫ ከፍ አድርጓል። ከ61 ዓመት በኋላ ተመሳሳይ ታሪክ ሊደገምበት የሚችልበት እድል አለ። 

ናፖሊ ከዚህ ቀደም የሴሪ አ ዋንጫን ሶስት ጊዜ አንስቷል።  ኢንተር ሚላን  20 ጊዜ የዋንጫው ባለቤት ሆኗል። 

የጣልያን ሴሪ አ ዋንጫ ወዴት ያመራል ወደ ኔፕልስ ወይስ ወደ ዋና ከተማዋ ሚላን? የሚለው ጉዳይ የዓለም እግር ኳስ አፍቃሪያን መነጋገሪያ ሆኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም