የዋንጫ ተፎካካሪዎቹ ኢትዮጵያ መድን እና ኢትዮጵያ ቡና የሚያደርጉት ተጠባቂ ጨዋታ - ኢዜአ አማርኛ
የዋንጫ ተፎካካሪዎቹ ኢትዮጵያ መድን እና ኢትዮጵያ ቡና የሚያደርጉት ተጠባቂ ጨዋታ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 15/2017 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 31ኛ ሳምንት የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን እና ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ የእግር ኳስ ተመልካቹን ትኩረት ስቧል።
የ31ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጀመራል።
በዕለቱ ከሚደረጉት ጨዋታዎች መካከል ኢትዮጵያ መድን እና ኢትዮጵያ ቡና ከምሽቱ 12 የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
ኢትዮጵያ መድን በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው 28 ጨዋታዎች 18 ጊዜ ሲያሸንፍ 4 ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። 6 ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።
38 ግቦችን ሲያስቆጥር 12 ግቦችን አስተናግዷል። በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የሚመራው መድን በ60 ነጥብ አንደኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ ባካሄዳቸው 28 ጨዋታዎች 15 ጊዜ ሲያሸንፍ 7 ጊዜ ተሸንፏል። 6 ጊዜ አቻ ወጥቷል።
በጨዋታዎቹ 26 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 14 ግቦችን አስተናግዷል። በነጻነት ክብሬ የሚሰለጥነው ኢትዮጵያ ቡና በ51 ነጥብ 2ኛ ደረጃን ይዟል።
ቡድኖቹ የሚያደርጉት ጨዋታ በዋንጫ ፉክክሩ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው መርሃ ግብር ነው።
በሌላኛው የ31ኛ ሳምንት መርሃ ግብር አስቀድሞ ከሊጉ መውረዱ የተረጋገጠው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከአርባምንጭ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ14 ነጥብ የመጨረሻውን 18ኛ ደረጃን ይዟል። አርባምንጭ ከተማ በ35 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
የ31ኛ ሳምንት መርሃ ግብር እስከ ግንቦት 18 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል።