ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጥያቄ የቀይ ባህርና የኤደን ባህረ ሰላጤን ደህንነት የማስጠበቅና የጋራ ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ጉዳይ ነው

አዲስ አበባ፤ግንቦት 14/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጥያቄ የቀይ ባህርና የኤደን ባህረ ሰላጤን ደህንነት የማስጠበቅና የጋራ ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ጉዳይ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተወካይና የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍጹም አረጋ ገለጹ።

3ኛው የቀይ ባሕር ቀጣናዊ ጂኦ-ፖለቲካ "የቀይ ባህር እና የኤደን ባህረ ሰላጤ ቀጣና አገራት ለኢኮኖሚያዊ፣ ለደኅንነት ትብብር እንዲሁም መልካም አጋጣሚዎች፣ ተግዳሮቶች እና የቀጣይ አቅጣጫዎች" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።


 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን በመወከል መልዕክት ያስተላለፉት የዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍጹም አረጋ የቀጠናው አገራት ከረጅም ዓመታት ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ያላቸው አገራት መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትብብሮችን ከማጠናከር ባለፈ የቀጠናውን ደህንነት በጋራ ማስጠበቅ ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የቀይ ባሕርን ደኅንነት ከማስጠበቅ አኳያ የባህር ላይ ዝርፊያዎችን ጨምሮ ሌሎች ሕገ-ወጥ ተግባራትን ለመከላከል የሚኖራት አስተዋጽኦ ትልቅ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጥያቄ የቀይ ባህርና የኤደን ባህረ ሰላጤን ደህንነት የማስጠበቅና የጋራ ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ጉዳይ እንደሆነም አንስተዋል።

ለዚህም በዲፕሎማሲያዊና በሰጥቶ መቀበል መርህ የባህር በር አጀንዳዋን ለማሳካት እየሰራች ነው ብለዋል።


 

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የቀይ ባሕር አካባቢን የጂኦ-ፖለቲካ ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ የቀጣናው አገራት ትብብር ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል።

የቀይ ባህርና የኤደን ባህረ ሰላጤ የቀጠናውን የንግድ ግንኙነት፣ የባህልና የእምነት ትስስር የሚያጠናክሩ፤ ኢኮኖሚያዊ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ናቸው ብለዋል።

የቀይ ባህር ቀጠናዊ ሉአላዊነትን የሚያስጠብቅ፤ የአካባቢውን ሰላም የሚያረጋግጥ ሁለተናዊ ብልፅግናን ለማምጣት ስትራቴጅክ የንግድ መስመር መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በቀጠናው ሰላምን ለማረጋገጥ፣ኢኮኖሚያዋ ትብብርን ለማሳደግ፣ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እየሰራች መሆኑንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጥያቄ የብሔራዊ ህልውናዋን የማስቀጠልና ቀጣናዊ የጋራ ብልፅግናን የማረጋገጥ የስትራቴጂካዊ ግቦቿ አካል እንደሆነም ዋና ዳይሬክተሩ አፅንኦት ሰጥተዋል።

በቀይ ባህርን እና የኤደን ባህረ ሰላጤ የባህር በር የማግኘትና በፍትሐዊነት የመጠቀም መብት እንዳላት ጠቅሰው፣ ይህን ለማሳካትም የተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች ብለዋል።

የቀይ ባሕር አካባቢን የጂኦ-ፖለቲካ ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ የቀጣናው አገራት ትብብር ወሳኝ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የቀጣናውን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ፣ የመሰረተ ልማት ትስስርና የኢኮኖሚ ውህደትን ለማፋጠን ከአካባቢው አገራት ጋር በትብብር እየሰራች ነው ብለዋል።


 

የመከላከያ ትምህርትና ስልጠና ዋና መመሪያ ሃላፊ ሌተናል ጀነራል ይመር መኮንን ከቀጠናው ተለዋዋጭ ሁኔታ የተነሳ ለቀጠናው ሰላም የጋራ ትብብር ሊጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄዋን በሰላማዊ መንገድ ለማሳካት እየሰራች መሆኑን ጠቅሰው፤ የአካባቢው ሰላምና ደህንነት እንዲረጋገጥ አገሪቱ ከረጅም ዓመታት አንስቶ እየሰራች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

በተለያዩ አገራትም በሰላም ማስከበር ተግባር በመሰማራት ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ እየሰራች መሆኑን አውስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም